የፍትሕ ያለህ!!

0
460

በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ‹‹የፍትህ ያለህ›› ያልተባለባቸው አጋጣሚዎችን ማስታወስ በእጅጉ ከባድ ስራ እንደሚያደርገው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ይህ ጉዳይ ታዲያ በየዘመናቱ እና በየአገዛዙ ቅርጹን ይለያይ እንጂ ሕዝብ ያልጮኸበት እና መንግሥትም ሲያስፈልገው የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ ሲጠቀምበት፤ በል ሲለው ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሲያልፈው በሕይወት ያሉ ሲነግሩን ከዛ ባሻርም በመጽሐፍት ላይ ተሰከትቦ የታሪክ ድርሳናት ላይ የሚገኝ ነገር ነው።

ይህ ታዲያ ሲንከባለል እና አሁንም ቅርጹን ቀይሮ መንግሥት ሔዶ ሌላኛው ሲመጣ የማይቀያየረው የሕዝብ ለቅሶ እና የፍትህ ያለህ ጩኸት አሁንም እንደቀጠለ ለመሆኑ በተለያዩ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቱን አውጥቶ አገር ጉድ ብሎ ሳይጨርስ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ሌላ አስደንጋች መረጃዎችን ይዞ ብቅ ይላል በዚህም መሐል ተጎጂውም ብቻ ሳይሆን የትኛውም ሰብዓዊው ዜጋ ከመንግሥት ፍትህን ሲጠብቅ የውሃ ሽታ ሆነው ሲቀሩ የታዘበበት ጊዜያት ሩቅ አይደሉም አሁንም እየታዘብናቸውም እንገኛለን። በመልካም አስተዳደር ብልሹነት የፍትህ ያለህ ሲባል፣ ራሱኑ በደል ቅርጹን ቀይሮ በሙስና ጉዳይ ብቅ ብሎ ሕዝብን ሲያስነባ ቀናት ሔደው ቀናት ይተካሉ መንግሥታትም ከእነ ጉድፋቸው ‹‹ምኑ ላይ ይሁን ችግሬ›› ሳይሉ ግብዓተ መሬታቸው ይፈጸማል።

ያለፉትን ለታሪክ ክስ እና ተወቃሽነት እንተዋቸው እና የአሁን ላይ ዘመናችንን ግን አሁንም የፍትህ ያለህ፤ ፍትህ ይረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በአገረኛ ብሒል የዘገየ ፍርድ እንደቀረ ይቆጠራል ቢልም ቅሉ ዘግይቶ እንኳን ይምጣልኝ የሚባለውን ትክክለኛውን ፍትህ ግን አሁንም ሕዝብ እየጠበቀ ይገኛል። ይህ ደግሞ የስልጣን ባለቤት ነህ የተባለውን ሕዝብ ሆድ ማሻከር ነው እና የሚሆነው በአስቸኳይ ከቀዳሚዎቹ በመማር ፍትህ ሊረጋገጥ ይገባል። ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በኩል አዳዲስ መስለው የቀረቡ ነገር ግን ከጊጊያት ወዲህ ወጥተው የከተማው መነጋገሪያ የነበሩ መረጃዎች ተሰራጭተው ነበር። የከተማ አስተዳደሩም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ የህገወጥ የመሬት ወረራ፣ህገወጥ ግንባታ ፣የጋራ መኖሪያ ቤት የማስተላለፍ ሂደት እና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ከቀበሌ ቤት አስተዳደር ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማጥራት በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ዝርዝር ጥናት በማካሄድ የጥናቱን ግኝት በጥር 18/2013 ዕለት ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የጥናቱን ግኝት ይፋ ያደረጉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከማዕከል ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳ ቤቶች ልማት ጽ/ቤቶች በተገኘ መረጃ መሰረት አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚተዳደሩ 150ሺህ 737 የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ያሉ ቢሆን በዚህ ጥናት ግን ተደራሽ መሆን የቻሉት 138 ሺህ 652 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ በከተማዋ 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባት እና በሌሎች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ መያዙን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥም 7ሺህ 723 ቤቶች ውል በሌላቸው (ህገወጥ) በሆኑ ሰዎች ተይዘዋል ብለዋል፡፡
2ሺህ207 የቀበሌ ቤቶች ደግሞ ወደግል የዞሩ፣ 265 በሶስተኛ ወገን የተያዙ እና 164 ኮንዶሚኒየም በደረሳቸው/የራሳቸው ቤት ባለቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ነውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፣1ሺህ 243 ታሽገው/ተዘግተው የተቀመጡ፣ 5ሺህ 043 የፈረሱ እና 180 አድራሻቸው የማይታዎቁ/የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ ፡፡

የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተም በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25,096 ናቸው ያሉት ወ/ሮ አዳነች ከነዚህ ውስጥ 4 ሺህ 076 በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

1ሺህ 070 የንግድ ቤቶች ውል የሌላቸው ነጋዴዎች እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ተለይቷል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ 2ሺህ 451 የቀበሌ የንግድ ቤቶች ከአንድ በላይ የንግድ ቤት 1,086 ነጋዴዎች እንደተያዙም ጥናቱ ያመላክታል ብለዋል፡፡

376 የቀበሌ ንግድ ቤቶች ደግሞ በተከራይ ተከራይ በሶስተኛ ወገን የተላለፉ እንዲሁም 179 የታሸጉ የንግድ ቤቶች እንዳሉም በጥናቱ ለመለየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈፀመው በህብተሰቡ ውስጥ ነው ያሉት ወ/ሮ አዳነች ህብረተሰቡ መሰል ህገወጥ ተግባራትን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ በተግባሩ የተሳተፉ አካላትን በማጋለጡ በኩል ሚናውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ ጉዳይ ታዲያ መቼ ነው ዕልባት የሚገኙት? ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኩል በከተማ ዋላ ይ የተሰራው የሕገ ወጥ የመሬት ቅርምት እና ዜጎችን ያለአግባብ የለፉበት ሲወሰድባቸው እና ለፍትህ ሲጮኹ የፍትህ ያለህ ሲባል በአደባባይ የተመለሰ ፍትህ ማየት አልተቻለም። ፣በመሆኑም መንግሥት በአስአቸኳይ የዜጎችን ዕንባ የሚብስ እና ፍትህ ለተጓደለባቸው እንዲቆም አዲስ ማለዳ በጽኑ ሀሳቧን ታስተላልፋለች። ከላይ የተያዙት እና በጥናት የተረጋገጡት መሬቶች እና መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ለዘመናት ኖሮ አሁንም በኪራይ እየተሰቃየ እና ለረጅም አመታት ከነገ ዛሬ ላገኝ እችላለሁ በሚል በተስፋ ለሚኖረው በፍትሀዊነት እና ሕግን በተከተለ መልኩ ሊተላለፍለት ይገባል፤ መሬቶቹም በትክክል ወደ መሬት ባንክ ገብተው ሊመዘገቡ እና የመንግስት ሀብትነታቸው በትክክል ሊረጋገጥ ይገባል። ምክትል ከንቲባዋ ይህን ጥናት ለመገናኛ ብዙኃን ያስታውቁ እንጂ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ጉዳዮን በሚመለከት የተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች ጭራሹኑ እርምጃ እንኳን ሊወሰድባቸው ቀርቶ በከተማ ፖሊሶች ጭምር ሲጠበቁ የታዘበችባቸውም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ አሁንም በሕዝብ ዝነድ ቂም እንዲቋጠር ማድረግ ነው እና በአስቸኳይ እንዲፈታ አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች። ይህ ታዲያ መሬት እና ቤት ጉዳዮችንም ብቻ ሳይሆን በሌላው ሴክተር ላይም ፍትህን ለተጠሙ እና ተቋምን እንገነባለን ከሚል መንግስት የሚጠበቀውን ትክክለኛ እና ሕጋዊ አካሔዶችን በማስፈን የፍትህ ያለህ እያለ ለሚጮኸው ሕዝብ ጥያቄው እንዲመለስለት በጥብቅ ታሳስባለች። አገርን አጽንቶ ትውልድን ለመገንባት እና ያለፈ ፤ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የፍትህ ጥያቄም በዚሁ ወቅት እንድናደርቀው ይሁን ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ታስታውቃለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here