ከወጪ ንግድ ከትግራይ በወር የሚገኘው 40 ሚሊዮን ዶላር ታጥቷል

0
554

በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ትግራይ ክልል ከህግ ማስከበር ሂደቱ በፊት በወር ከውጪ ንግድ 40 ሚሊዮን ዶላር ታገኝ እንደነበር እና ከህግ ማስከበሩ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት መቋረጡ በየወሩ 40 ሚሊየን ዶላር እንደሚታጣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በህግ ማስከበሩ ጊዜ አገራችን ከትግራይ ክልል ከውጪ ንግድ ታገኝ የነበረውን 40 ሚሊየን ዶላር ከህግ ማስከበር ጊዜው ጀምሮ ማግኘት እንዳቆመች አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። ከክልል ለውጪ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ ወርቅ እንዲሁም ጥጥ ይገኙበታል።

በትግራይ ክልል ከህግ ማስከበሩ ጋር በተያያዘ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንደተጎዳ እና በዚህም ከ50 እስከ 90 በመቶ የሚደርስ ጉዳት ኢንቨስትመንቱ ላይ እንደደረሰበትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ዮሀንስ ድንቃየሁ ከኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በአገራችን የተለያየ ጊዜ በተፈጠሩ ግጭቶች አገራችን ላይ ባሉ በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በዚህም ውድመት ከደረሰባቸው ኢንቨስትመንቶች መካከል መመለስ የሚቻለው አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ከዚህ ቀደም አሳውቀው እንደነበር ይታወሳል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የኢኮኖሙ ባለሙያ ዋሲሁን በላይ እንደተናገሩት እንደ ኢትዮጵያ ላለች በማደግ ላይ ያለች አገር ቀርቶ ያደጉ አገራትንም ቢሆን ጦርነት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የሚከት አገርን የሚጎዳ የኢኮኖሚዋንና እድገቷን የሚጎዳ እንዲሁም ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ብለዋል።

እንደ አገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳለብን ይታወቃል በዚህም ትግራይ ክልል ከውጪ ንግድ ይገኝ የነበርው 40 ሚሊየን ዶላር ከማጣትም በላይ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬን የሚጠይቁ የማቋቋሚያ ስራዎች ይጠብቀናል ሲሉ ተናግረዋል።

ትግራይ ክልል ላይ የተነሳው ችግር የሚጎዳው የትግራይ ክልልን ብቻ አይደለም እንደ አገር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከትላል ብለዋል።
ከህግ ማስከበር ሂደቱ በኋላ የሚኖረውን ውጥረት ለመፍታት መንግስት ከሌሎች ክልሎች በጀት ላይ ነው የሚያነሳው ይህ ደግሞ በራሱ ጉዳቱ እንደ አገር እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።

በህግ ማስከበሩ ጊዜ መንግስት የተለያዩ ወጪዎችን ሲያወጣ ነበር አሁንም የህግ ማስከበሩ ከተጠናቀቀ በኋላም የተሰደዱትን ሰዎች ከመመለስ ፣ ከማቋቋም እንዲሁም የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን አገር እንደ አገር ከምታጣው በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪም ይጠይቃታል ብለዋል።

በተለይም የቱሪዝም መዳረሻም የሆነ ክልል ጭምር ነው።በዚህም ጦርነት ሲኖር የውጪ አገር ዜጋ አይኖርም ይህ ካልሆነ ደግሞ የውጪ ምንዛሬ አይገኝም የውጪ ምንዛሬ ለአንድ አገር እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታወቃል በዚህም የአገር እድገትንም ጭምር ያጓትታል ብለዋል።

በዋናነት የሰውን ሰላም መልሶ ማቋቋም የመጀመሪያው ስራ ነው ያሉት ኢኮኖሚስቱ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ካወጣው ወጪ ይልቅ በርከት ያለ ገንዘብ ማውጣት ይጠበቅበታል ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ ቀድሞ የሰውን ሰላም ማረጋገጥ አለበት በዚህም አሁን የያዘውን ተልዕኮ ቶሎ በማጠናቀቅ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም አለም አቀፍ ተቋማቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠይቆ የሰብአዊ ድጋፍ ቶሎ እንዲደርስ መደረግ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።
በቀጣይም በአነስተኛ ወለድ የሚከፈሉ የረጅም ጊዜ ብድር በመውሰድ የመሰረተ ልማቱን መጠገን አለበት።መንግስት ላይ ከፍተኛ ስራ ይጠበቃል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጥቅምት 24 ቀን ጀምሮ በትግራይ ክልል ከተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆና መቆየቷ እና አሁን በከፊል እንቅስቃሴዎች እየተጀመሩ መሆናቸው ይታወቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here