የመረጃ ነጻነት እና ሕዝባዊ ተሳትፎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሒደት

0
1189

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

በሚኪያስ በቀለ (አምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1. የመረጃ ነጻነት- ሕጋዊ ዳራ
የመረጃ ነጻነት ከሦስቱ አንዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ የሰብኣዊ መብት አካል ነው። ሌላዎቹ ኹለቱ፤ ሐሳብን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመግለጽ እና አመለካከት የመያዝ መብቶች ናቸው። ይህ የሰብኣዊ መብት ኢትዮጵያ አባል በሆነችባቸው የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተደንግጎ ይገኛል። የዓለም ዐቀፍ የፖለቲካ እና የሲቪል መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(2)፣ የአፍሪካ የሰብኣዊ እና ሕዝቦች መብት ቻርተር አንቀጽ 9 ብሎም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ዜጎች መረጃን የማግኘት መብት እንዳላቸው ያትታሉ።

የዜጎች ከመንግሥታዊ ተቋማት መረጃ የማግኘት መብት የሕግ ፍልስፍናዊ መሠረቱን የሚያገኘው ተቋማቱ ካላቸው ሕዝባዊ ባህሪ እና የመረጃው ባለቤት አንጻር ነው። ይህም ማለት ተቋማቱ የሚኖሯቸው መረጃዎች የራሳቸው ሳይሆኑ፣ ዜጎችን በመወከል የያዟቸው ናቸው። ስለዚህ ዜጎች የሚጠይቁት የራሳቸውን መረጃ በመሆኑ ተቋማቱ በማንኛውም ጊዜ የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።

መረጃ የማግኘት ነጻነት እንደ ሰብኣዊ መብትነቱ መንግሥት ያለበት ኃላፊነት አንዱ “መብቱን አለመጣስ” ሲሆን፤ ኹለቱ ደግሞ የማስፈጸም (ክልከላዎችን የመቆጣጠር) እና የሟሟላት (መብቱ የሚተገበርበትን የሕግ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ የማኖር) ግዴታዎች ናቸው።

ዜጎች በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ከሚኖራቸው ተሳትፎ አንጻር የመረጃ ነጻነት ሊታይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ዜጎች ለተሳትፎ ጥሪ ሲደረግላቸው ለዝግጅት ከሚሰጣቸው ጊዜ እና የመረጃ ይዘት አንጻር ነው።

2. በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ለሚደረግ ሕዝባዊ ውይይት መረጃ የሚሰጥበት ጊዜ – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሞክሮ
ለተሳታፎ የሚደረግ ጥሪ እና መረጃ መሰጠት ያለበት ከውይይቱ ቀደም ብሎ መሆን አለበት። ዜጎች ከባለሙያ ጋር መመካከርን ጨምሮ ለዝግጅት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ጊዜ ማግኘት አለባቸው። መረጃን ቀደም ብሎ ማግኘት የተለያዩ ቡድኖችን የሚወክሉ የሲቪክ ማኅበራትም ባለሙያ አማክረው፣ ከሚወክሉት ማኅበረሰብም ጋር ተመካክረው እንዲዘጋጁ እና ጠቃሚ፣ ማኅበረሰቡንም የሚወክል አስተያየት ይዘው እንዲመጡ ያግዛል። ይህም ዜጎች በተሻለ ስለሚወጣው ሕግ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ጠቃሚ ሐሳብ እንዲያጋሩና በሕግ አወጣጥ ሒደት ውስጥ ተገቢውን ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ያደርጋል።

ከውይይት በፊት ለዝግጅት የሚያስፈልገው ጊዜ ወጥነት ባይኖረውም፣ ከረቂቅ ሕጎች አዲስነት፣ ስፋት፣ እና ሕጉ በሀገር እና ማኅበረሰቡ ላይ ከሚያመጣው ውጤት አንጻር መታየት ይኖርበታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የረቂቅ ሕጉን የሚመለከቱ መረጃዎች በተለያዩ አማራጮች ለማሳወቅ ሙከራ ይደረጋል። ሰፊው ዜጋ በሕጎች ላይ ቀርቦ እንዲሳተፍ እና ሐሳቡን እንዲያቀርብ ጥሪ የሚደረገው በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ነው። ምክር ቤቱ በዋነኛነት በሀገሪቷ ተደራሽ በሆኑት የኢትዮጵያ ቴሊቭዥንን እና በ97.1. ኤፍ ኤም ላይ የሚደመጠውን ሬዲዮ ይጠቀማል። የተሳትፎ የማስታወቂያ ጥሪው የሚተላለፈው ማኅበረሰቡ ሊሰማው ይችላል ተብሎ በሚታሰብበት ሰዓት ሲሆን፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይተላለፋል።

አብዛኛውን ጊዜ የሚዲያ ጥሪው የሚደረገው ከውይይቱ ከሦስት እስከ አምስት ቀናት በፊት መሆኑን የምክር ቤቱ የሚዲያ ዳይሬክተር ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያስረዳሉ። እንደ ዳይሬክተሯ አገላለጽ አንዴ ብቻ ከ10 ቀናት በፊት የሚዲያ ጥሪ መደረጉን ያስታውሳሉ። የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የሕግ ባለሙያ ለውይይት ዝግጅት የሚሰጠው ጊዜ በቂ አለመሆኑ ከመግለጽ አይቆጠቡም። በሚያስገርም ሁኔታ የሚዲያ ዳይሬክተሯ የጥሪው ማስታወቂያ የሚነገርበት ጊዜ ሳይጠናቀቅ የውይይቱ ጊዜ የደረሰበት ጊዜ እንደነበረም ያስታውሷሉ። የቋሚ ኮሚቴዎች ወጥ የሆነ አካሄድ ከመሄድ ይልቅ ውይይት የሚደረግባቸው ረቂቅ ሕጎችን ጥልቀት፣ አዲስነት እና ከሚኖራቸውን ውጤት አንጻር ለተሳታፊዎች ዝግጅት የሚሰጡትን ጊዜ ቢወስኑ ይመከራል።

3. በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ለሚደረግ ሕዝባዊ ውይይት የሚሰጠው መረጃ ይዘት – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሞክሮ
ዜጎች በሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ ከመሳተፋቸው በፊት የሕጉን ረቂቅ እና ተያያዥ ሰነዶችን ቢያገኙ ይመከራል። መረጃ ከሚወጣው ሕግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የተሳትፎውን አካሄድ፣ ተሳትፎ የሚካሄድበትን ቀን እና ቦታም በግልጽ ማካተት ይኖርበታል።

ለተሳትፎ የሚደረግ ጥሪ ስለ ረቂቅ ሕጉ በቂ የሆነ መረጃ ማቀበል ይኖርበታል። ረቂቅ ሕጉን፣ ሕጉን ለማርቀቅ ምክንያት የሆኑ ኩነቶች እና በዝግጅት ጊዜ የነበሩ ሰነዶች በተወያዮች ቢገኙ የተሻለ ይሆናል።

ሀ) በሚዲያዎች የሚደረጉ ጥሪዎች
የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ለሕዝባዊ ተሳትፎ የሚደረገው ጥሪ ስለ ረቂቅ ሕጉ የሚሰጠው መረጃ ትንሽ መሆኑን ይገልጻሉ። አክለውም የረቂቅ ሕጉ ዓላማ እና የሚኖረው ውጤት በአጭሩ ቢገለጽ የተሻለ እንደሚሆን ይናገራሉ።

ከሚዲያ ጋር ውል በመዋዋል የተሳትፎ ጥሪዎቹ እንዲተላለፉ የሚያመቻቸው የምክር ቤቱ አካል ኃላፊ የሆኑት የምክር ቤቱ ጽ/ቤት የሚዲያ ዳይሬክተር በበኩላቸው፥ የተሳትፎ ጥሪው ይዘት ውይይቱን የሚያዘጋጀው ቋሚ ኮሚቴ እንጂ የሚዲያ ክፍሉ ኃላፊነት እንዳልሆነ ይገልጻሉ። እንደ ሚዲያ ዲያሪክተሯ አገላለጽ ቋሚ ኮሚቴዎች ውይይት የሚካሄድበትን ረቂቅ አዋጅ እና ከየትኛው ጠቅላላ ጉባኤ እንደተመራ ያካተተ ደብዳቤ እንደሚልኩላቸው እና ይህንኑ በሚዲያ እንዲተላለፍ በቀጥታ እንደሚልኩ ይገልጻሉ።

የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑ የፓርላማ አባል በሚዲያ በሚደረገው ጥሪ ላይ ስለ ረቂቅ አዋጆች ያለው ይዘት አነስተኛ መሆኑን አምነው፣ ግን ማኅበረሰቡ በመጀመሪያ ንባብ በነበረው ውይይት ስለ ረቂቁ ግንዛቤ ስለሚያገኝ ይዘቱን ማስፋት ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ። ነገር ግን ይህ አባባል ሁሉም ለመሳተፍ ፍላጎቱ ያላቸው እና ባለድርሻ አካላት የጠቅላላ ጉባኤውን ይመለከታሉ ከሚል ግንዛቤ የሚመነጭ ይሆናል። የተመረጡ እንጂ ሁሉም ጠቅላላ ስብሰባዎች በሚዲያ አለመተላለፋቸውም የሊቀ መንበሩን እይታ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። የጠቅላላ ጉባኤ ውይይቶች የሚተላለፉበት አካሄድም ለሕዝባዊ ውይይት ዝግጅት ለማድረግ በሚያመች መልኩ አይሆንም።

ለ) በምክር ቤቱ ድረ ገጽ
በጥናቱ ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የምክር ቤት አባላትም ሆኑ የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ረቂቅ ሕጎች በምክር ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ስለሚገኙ ከዚያ ላይ ተመልክቶ መዘጋጀት እንደሚቻል ይናገራሉ። ነገር ግን የምክር ቤቱ ድረ ገጽ (www.hopr.gov.et) የማይሠራበት ብዙ ጊዜ ነው። የምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር የምክር ቤቱ ድረ ገጽ በተለያዩ ጊዜያት ላለመሥራቱ የቴክኒክ ጉዳይ ያነሳሉ። መፍትሄ በማፈላግ ሥራ ላይ መሆናቸውንም ያክላሉ።

ድረ ገጹ አለመሥራቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ረቂቅ ሕጎችም አይቀመጡም። የኢንፎርሜሽን ዲያሪክተሩ ሁሉም ረቂቅ ሕጎች ለምን በድረ ገጻቸው ላይ እንደማይቀመጡ ሲያስረዱ የቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ ሕጎችን ስለማይልኩ ወይም ዘግይተው ስለሚልኩ መሆኑን ይገልጻሉ። ረቂቅ ሕጎች እንደልብ በድረ ገጽ አለመገኘታቸው የተለያዩ አካላት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ምክንያት መሆኑን የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በቋሚ ኮሚቴዎች እና በኢንፎርሚሽን ቴክኖሎጂ የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ክፍል መካከል በመመሪያ ላይ የተመሠረተ ወጥ የሆነ ግንኙነት ሊፈጠር ያሻል።

እንደ ምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ አገላለጽ የውይይት ተሳታፊዎች ብዙውን ጊዜ ረቂቅ አዋጆች የሚደርሷቸው ለተሳትፎ በመጡበት ጊዜ እዛው በአዳራሹ ውስጥ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም የውይይት ተሳታፊዎች በቂ ዝግጅት አድርገው እና ተዘጋጅተው፣ ጠቃሚ ግብዓትም ይዘው እንዳይመጡ ምክንያት ይሆናል።

ሐ) በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች
በሀገሪቷ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ማደጉን ተከትሎ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ተጠቃሚ በሀገሪቷ እየጨመረ ነው። የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የማኅበራዊ ሚዲያዎችን የመጠቀም አዝማሚያ እያሳዩ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ለመጠቀም እንዲችል የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን የሚያስተዳድር የራሱን ክፍል አቋቁሞ፤ የፌስቡክ፣ የትዊተር እና የዩቲዮብ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ዘዴዎችን ይጠቀማል። ነገር ግን የሕዝባዊ ተሳትፎ ጥሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲገለጹ አይስተዋልም። ይልቁንም የጠቅላላ ጉባኤ ለዝርዝር ምርመራ ረቂቅ ሕጎችን ወደ ቋሚ ኮሚቴ ማስተላለፋቸውን ከአዋጁ ሥም እንዲሁም ሕዝባዊ ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላም እንደ ዜና ሆነው ይቀርባሉ።

መ) ለባለድርሻ አካላት ቀጥታ ጥሪዎች ሲደረጉ
በመገናኛ ብዙኀን ከሚደረጉ ጥሪዎች ባሻገር ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት በደብዳቤ እና በኢሜል በቀጥታ በቋሚ ኮሚቴዎች ጥሪ ይደረግላቸውል። ይህንን ለማስፈጽም ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎቹ ቋሚ ኮሚቴዎች የራሳቸው ኦፊሰሮች እንዳላቸው የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ይገልጻሉ። የሕግ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ የመገናኛ ብዙኀን ጉዳዩች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑ የምክር ቤቱ አባል ረቂቅ አዋጆች በደብዳቤ ለሚጠሩ በወረቀት፣ በኢሜል ለሚጠሩ ደግሞ የኮንፒዩተር ኮፒ እንደሚላክላቸው ያስራዳሉ።

4. ቀጥታ የሚደረጉ ጥሪዎች – እንማን ይጠራሉ?
ቋሚ ኮሚቴዎች ሕዝባዊ ውይይት ላይ ተሳትፎ እንዲደረግ በመገናኛ ብዙኀን ጥሪ ከማድረጋቸው ባሻገር፤ ይመለከታቸዋል የሚሏቸውን አካላት በእራሳቸው በቀጥታ ጥሪ ያደርጋሉ። “ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው?” የሚለው ወጥ የሆነ ምላሽ የለውም። ለዚህ ጽሁፍ ጥቅም ግን ሰፋ ብሎ ማናቸውም ባለሙያ የሆኑ ወይም ባለሙያ ያልሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሆነው በሚወጣው ሕግ/ፖሊሲ ቀጥተኛ ተጠቂ የሆኑ ወይም በሒደቱ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን አካላት አካትቶ ሊተረጎም ይችላል።

የቋሚ ኮሚቴ ለባለድርሻ አካላት ጥሪውን የሚያደርገው በደብዳቤ ወይም በኢሜል ሊሆን ይችላል። በቀጥታ ጥሪ የሚደረግለት ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው ለሚለው ግን ወጥ የሆነ አሠራር የለም። የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ለዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ እንዳስረዱት ጥሪ የሚደረግላቸውን አካላት የመወሰን ኃላፊነቱ የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር እንደሆነ እና ከቋሚ ኮሚቴ ቋሚ ኮሚቴ ልዩነት መኖሩን ይገልጻሉ። የሌላ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር በበኩላቸው የሚወጣውን ሕግ የሚያስፈጽሙ አካላት ዋነኞቹ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን እና ለነሱ ጥሪ እንደሚደረግላቸው ይገልጻሉ። የሌላ ሦስተኛ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ደግሞ ብዙ ጊዜ በቋሚነት በቀጥታ የሚጠሩ ባለድርሻ አካላት መኖራቸውን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል በጥናቱ ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ከመንግሥት ጋር ንክኪ የሌላቸው እና የብዙ ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው የሲቪክ ተቋማት ኃላፊዎች በምክር ቤቱ ጥሪ እንደማይደረግላቸው ይገልጻሉ። በኦሮሚያ ክልል ለረዥም ጊዜ በልማት ስራዎች ላይ የሚንቀሳቀስ የሲቪክ ማኅበር ዳይሬክተር የተቋሙ ኃላፊ ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ በምክር ቤቱ በሕግ ላይ ውይይት እንዲደረግ በቀጥታ ጥሪ የቀረበላቸውን ጊዜ እንደማያስታውሱ ይገልጻሉ። በተመሳሳይ በሴቶች መብት ላይ የሚሠራ አንድ የሲቪክ ማኅበር ዳይሬክተርም ተቋማቸው በምክር ቤቱ ጥሪ ተደርጎለት እንደማያውቅ ይገልጻሉ። ለረዥም ዓመታት በሃይማኖት ዙሪያ የሚሠራ አንድ ሀገር በቀል የሲቪል ተቋም ኃላፊም ተመሳሳይ ሐሳብ ያቀርባሉ። የውጪ ዜግነት ያለው ወላጅ አልባ ሕጻናትን በማሳደግ ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ የዓለም ዐቀፍ የሲቪክ ተቋምም በተመሳሳይ በቀጥታ ምክር ቤቱ ጥሪ አድርጎላቸው እንደማያውቅ ይገልጻሉ። ከዚህም ማኅበረሰቡን በአንድ በኩል እና መንግሥትን እና የንግዱ ዘርፍ በሌላ በኩል የሚያገናኙ ድልድይ ተብለው የሚወሰዱት የሲቪክ ተቋማት እንደባለድርሻ አካላት ተገቢው ትኩረት እንደማይቸራቸው መረዳት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here