ከምርመራ ኦዲት ከተገኘው ገንዘብ ወደ ገቢ መቀየር የተቻለው ሰባት በመቶውን ብቻ ነው

0
668

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2013 ግማሽ በጀት አመት ሪፖርት ላይ ከምርመራ ኦዲት (ከታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ) ከተገኘው አንድ ቢሊየን 275 ሚሊየን 521 ሺሕ 309 ብር ላይ ወደ ገቢ መቀየር የተቻለው 95 ሚሊየን 340 ሺሕ 013 ብር ብቻ መሆኑን በዚህ የዕቅዱን ሰባት ነጥብ አራት ሰባት በመቶ ብቻ ማሳካት መቻሉን አስታወቀ።

ይህም የተገኘው በስድስት ወር ውስጥ ኦዲት ለማድረግ በዕቅድ የተያዘው በፋይል 258 ሲሆን ከእነሱ ውስጥ 213 የሚሆነው ፋይል ተመርምሮ እንደሆነ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ ተፈራ ተናግረዋል።

ቢሮው በ2013 ግማሽ በጀት አመት 24 ነጥብ 28 ቢሊየን ብር ታክስ ለመሰብሰብ አቅዶ 22 ቢሊየን 487 ሚሊየን ብር ወይም የእቅዱ 94.3 በመቶ ማሳካት እንደቻለ ቢሮው የግማሽ አመት ሪፖርቱ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ከቀጥታ ታክሶች ብር 17 ነጥብ ሦስት መቶ ሰባ አራት ቢሊየን ብር ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች ስድስት ነጥብ ኹለት መቶ 19 ቢሊየን ብር እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ብር 687 ነጥብ 35 ሚሊየን ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህም አፈፃፀሙ ከቀጥታ ታክስ 17 ነጥብ 533 ቢሊየን ፣ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ 5 ቢሊየን እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 349 ነጥብ 54 ሚሊየን መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ቢሮው ሪፖርቱን በሚያቀርብበት ወቅት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊው በግማሽ አመቱ ከታክስ የተገኘው ገንዘብ ከአለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ስድስት በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ በዚህም በብር ሲሰላ የአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ብር እድገት ማየቱን ጠቁመዋል።

የግብር ታክስ ተመላሽ አፈፃፀምን በተመለከተ በበጀት አመቱ ግማሽ የ268 ግብር ከፋዮች አምስት መቶ 26 ነጥብ 25 ሚሊየን ብር ጥያቄ ተጣርቶ 337 ነጥብ 75 ሚሊየን ብር በገንዘብ ተመላሽ መሆኑን ተናግረዋል።

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ ቢሮው ከተለያዩት ቅርንጫፎቹ 96 የሚሆን የቁጥጥር ስራውን የሚሰራ ብድን አዋቅሮ እንደተንቀሳቀሰ እና በዚህም 130 ሺሕ 204 የሚሆኑ የንግድ ቤቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ 121 ሺሕ 692 የንግድ ቤቶች ላይ ቁጥጥር ማድረጉን በዚህም የእቅዱን 93 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ቁጥጥር ከተደረገባቸው የንግድ ቤቶች ላይ 99 ሺሕ 240 ቤቶች መመዝገቢያ ማሽኑን በአግባቡ የሚጠቀሙ ሲሆኑ 22 ሺሕ 452 የሚሆኑት ግብር ከፋዮች ላይ ክፍተቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በስድስት ወሩ ኹለት ሺህ አንድ መቶ 79 ግብር ከፋዮች ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት ተትሎባቸዋል በዚህም 79 ሚሊየን ብር ማግኘት ተችሏል።
በሌላ በኩል የጣት አሻራ መስጠትን በተመለከተ በስድስት ወር ለ57 ሺሕ አንድ መቶ ለሚሆኑ ተገልጋዮች ለመስጠት ታቅዶ 80 ሺሕ ስድስት መቶ ሰማኒያ ስምንት ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎቱን መስጠት እንደተቻለ በዚህም የእቅዱን 141 ነጥብ 11 ለማከናወን እንደተቻለ አሳውቀዋል።

ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ከፍለው ሲጨርሱ የሚሰጣቸውን ክሊራንስ በተመለከተ ኹለት መቶ 64 ሺሕ 596 ሰዎች መውሰድ ሲኖርባቸው ኹለት መቶ 51 ሺሕ 423 የሚሆኑ ነጋዴዎች መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በስድሰት ወራት ውስጥ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው በዋናነት በያዝነው በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ የገጠማቸው ተግዳሮቶች መካከል ሀሰተኛ ደረሰኞች መበራከት ዋናው እንደነበር ተናግረዋለው ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here