የአማራ ክልል ተቋራጮች በልማት ድርጅቶች ምክንያት ከሥራ ውጭ መደረጋቸውን አስታወቁ

የአማራ ክልል የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ማሕበር በክልሉ የሚገኙ የግል ተቋራጮች(ኮንትራክተሮች) በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምክንያት ከሥራ ውጭ እየሆኑ ነው በማለት የማሕበሩ ፀሐፊ አለም ፈንታ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የአማራ ክልል ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማሕበር አሁን በተለያዩ ምክንያቶች ማሕበሩ በሚገባ እየተንቀሳቀሰ ባይሆንም ሕጋዊ እውቅናው ግን መታደሱን አሳውቀው አሁን ላይ 166 ያህል አባላት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የማሕበሩ ፀሀፊ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኮንትራክተር ብቻ ሳይሆኑ አማካሪ ድርጅትም አላቸው። እንደ ምሳሌ የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራሽን ድርጅትን ብንወስድ ለመሥራት የተቋቋመው ውሃ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ቢሆንም አሁን ግን ሕንጻ በመሥራት ላይ ይገኛል ከዚህ በተጨማሪም አልማ አልማኮ የተባለ የራሱ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የሚሠራ ድርጅት አለው። እነዚህ ድርጅቶች ለምን የግንባታ ፍቃድ አወጡ ሳይሆን ለምን ከእኛ ጋር እኩል ጨረታ አይሳተፉም የሚል ጥያቄ እንዳላቸው ተናግረዋል።

አክለውም ይህ ጥያቄ ዛሬ ላይ ብቻ የተነሳ ሳይሆን ገዱ አንዳርጋቸው የክልሉ ርዕሰ መሥተዳደር በነበሩበት ወቅት እሳቸው ቢሮ ድረስ በመሄድ ጉዳዩን ማቅረባቸውን አስታውሰዋል። በወቅቱ ለክልሉ የሥራ እና የከተማ ልማት ቢሮ መመሪያ እንዲያወጣ እስከማዘዝ ደርሰው ነበር። በቃላት የሰጡን ምላሽ እስከ ታች ወርዶ አሁንም ድረስ መፍትሄ አላገኘም ብለዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የግንባታ ሥራዎችን ለመሥራ የተቋቋሙት ከኮንትራክተሮች አቅም በላይ ለሆኑ አስቸጋሪ እና በጣም ሩቅ ለሆኑ ቦታዎች ነው ምክንያቱም እነርሱ ከግል የግንባታ ተቋራጮች የተሻሉ ማሽኖች አሏቸው። አሁን ግን በትንንሽ ብር የሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ሁሉ ተሰማርተዋል ብለዋል። ይህ ችግር በግል የሚንቀሳቀሱ ኮንትራክተሮችን ጎድቷቸዋል። አንዳንዶቹ ከስረው ቤት እና መኪና እስከመሸጥ ደርሰዋል በማለት ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአማራ ክልል የሚሠሩ ተቋራጭ፤ በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የግንባታ ፈቃድ ስላላቸው በሚወጡ የግንባታ ጨረታዎች ሁሉ ይሳተፋሉ ብለዋል። አብዛኛዎቹ ጨረታዎች ውስን ሰለሆኑ የመጫረት እድሉን ሳናገኝ የመንግሥት ድርጂቶች ብቻ ይሳተፋሉ፤ ሥራውንም ይወስዳሉ። እንዲሁም የመንግሥት ተቋራጮች በየወሩ በደሞዝ የሚሰሩ በመሆናቸው የጊዜ እና የትርፍ ጉዳይ አያሳስባቸውም የግል ተቋራጮች ግን ሥራውን አጠናቀው ክፍያቸውን ለመውሰድ እና ሌሎች ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ እንዲረዳቸው ግንባታቸውን በቶሎ ያጠናቅቃሉ እንደ ባለሙያም ስመለከት ጥራታቸው ዝቅ ያለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብለዋል።

በአማራ ክልል ሥራ እና ከተማ ልማት ቢሮ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አስናቀ ይርጉ የኛ መሥሪያ ቤት ኃላፊነት የጨረታ ግዥዎችን ማስፈጸም እንዲሁም ለግል ሆነ ለመንግሥት ኮንትራክተሮች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ነው። እንደ ኀላፊ ሁሉም የጨረታ ግዥዎች በግልጽ መደረግ እንዳለባቸው አምናለሁ። የግል ተቋራጮች ሠራተኞች ቀጥረው የሚሠሩ በመሆናቸው ጨረታዎች ላይ ተሳትፈው ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸውም አምናለሁ በማለት ገልጸዋል።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና የመንግሥትም በመሆናቸው ከግንባታ መቋረጥ እና መጓተት ጋር የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍራት ብዙ ተቋማት ሥራዎቻቸውን ለእነዚህ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መስጠት ሊመርጡ ይችላሉ ይህ ተጠያቂነትን በመፍራት የሚደረግ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ከግንባታ ጥራት ጋር ለተነሱ ጥያቄዎች ግን እኔ የምረዳው በተቃራኒው ነው ከግል የግንባታ ተቋራጮች ይልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አማካሪ ባላሙያ ቀጥረው ስለሚሠሩ የጥራት ችግር አለባቸው ብየ አላምንም ሲሉ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here