ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም ላያንጸባርቅ ይችላል።
በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1) ሕዝባዊ ውይይቶች መች ይካሄዱ?
በሕግ ማውጣጥ ውስጥ የሚደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ብዙም ሳይቀድሙ ብሎም ሳይዘገዩ መካሄድ ይኖርባቸዋል። በጣም ከቀደሙ፤ ማለትም የቋሚ ኮሚቴው ሕጉን ለመመርመር ከመቀበሉ በፊት ከሆነ በሕዝባዊ ውይይት የሚቀርቡ ሐሳቦች ዋጋ ያጣሉ፣ ምክር ቤቱም ግምት ውስጥ ሊከታቸው አይችልም። በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ ድምጽ የሚሰጥበት የመጨረሻ ጊዜ ከደረሰ በኋላም ከሆነ በሕዝባዊ ውይይት ላይ የሚሰበሰቡ አስተያየቶች እንደ ግብዓት የመቆጠራቸው አጋጣሚ ይመነምናል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሰራር ሕዝባዊ ውይይቶች የሚካሄዱት የቋሚ ኮሚቴዎች በሚያደርጉት ጥሪ እና በሚያዘጋጁት መድረክ ነው። ረቂቅ አዋጆች ከአጠቃላይ ስብሰባ ለቋሚ ኮሚቴዎች ከተመራላቸው በኋላ በመጀመሪያ የሚያደርጉት ረቂቅ ሕጉን ከላከው መንግሥታዊ ተቋም ከሚመጣ ግለሰብ (አስረጂ) ጋር ውይይት ማድረግ ነው። ይህ ውይይት ብዙውን ጊዜ ለአንድ እና ኹለት ቀን እንደሚደረግ እና በዚህም ጊዜ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚታመን የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ለዚህ ጹሁፍ አቅራቢ ያስረዳሉ። ሕዝባዊ ውይይት (Public Hearing) የሚካሄደው ይህንን ተከትሎ ነው። የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሕዝባዊ ውይይት ከማካሄዳቸው በፊት ከአስረጂዎች/ባለሙያዎች ጋር የሚመካከሩት ስለ ረቂቅ አዋጁ ቀድመው ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሆኑን የጽሁፉ አቅራቢ ያነጋገሯቸው የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ይገልጻሉ።
ከአስረጂ እና ባለሙያዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች እንደሁኔታው ከሕዝባዊ ውይይት በፊት ወይም በኋላ ሊደረጉ እንደሚችሉ የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 167(4) ያስቀምጣል። የቋሚ ኮሚቴዎቹ ቀድመው ሕዝባዊ ውይይቱን ቢያካሂዱ ረቂቅ ሕጉን ከላከው ተቋም ከሚመጡ አስረጂዎች (ሹመኛም ሆኑ ባለሙያዎች) ጋር በሚኖራቸው ምክክር ከሕዝባዊ ውይይት ያገኟቸውን ሐሳቦች የማቅረብ፣ የመሞገት እና በረቂቅ ሕጎች ውስጥ እንዲካተቱ የመወትወት እድሉን ይሰጣቸዋል። ነገር ግን የቋሚ ኮሚቴው አስረጂዎችን በማንኛውም ጊዜ ጠርተው ማነጋገር ስለሚችሉ ከአስረጂዎች ጋር የሚደረገው ውይይት ከሕዝባዊ ተሳትፎ በኋላ መሆኑ አለበት የሚለው ክርክር ሚዛን እንደማይደፋ የምክር ቤቱ የጥናት ባለሙያ ይከራከራሉ። የቋሚ ኮሚቴዎች የሚላክላቸውን ረቂቅ ሕግ ለመመርመር የሚኖራቸው ጊዜ 20 ቀናት (በአፈ ጉባኤው ሊራዘም የሚችል) መሆኑ ግን በተደጋጋሚ አስረጂዎችን ለመጥራት በቂ ጊዜ ሊኖር የማይቻልበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል።
ከሕዝባዊ ውይይቶች በፊት ስለ ረቂቅ አዋጆች ግንዛቤ ለማግኘት በምክር ቤቱ ካሉ ወይም ከውጪ ከሚመጡ ባለሙያዎች ጋር ምክክር ማድረግ ይቻላል። እንደ ምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ አገላለጽ ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጅ እንደተላከላቸው ወደ ምክር ቤቱ ባለሙያዎች እንደሚልኩ እና ሐሳብ እንደሚጠይቁ፣ ለአስረጂዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችም እንደሚዘጋጁ ይገልጻሉ። ነገር ግን ለባለሙያዎቹ የሚሰጠው ጊዜ አጭር መሆኑን፣ የምክር ቤቱ ጽ/ቤትም የባለሙያ እጥረት እንዳለበት እና ቋሚ ኮሚቴዎች የውጪ ባለሙያዎችን የመጋበዝ ልምዱም እንደሌላቸው የሕግ ባለሙያ ይገልጻሉ።
2. ሕዝባዊ ውይይቶች እንዴት ይካሄዱ?
መድረኮቹ የሚመሩት ውይይቱን በጠራው ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ነው። የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ መንበር መድረኩን ከከፈቱ በኋላ፣ ረቂቅ ሕጉን ካቀረበው መንግሥታዊ ተቋም የመጣ አስረጂ ስለ ረቂቅ ሕጉ አስፈላጊነት እና ዋና ዋና ይዘት አጭር ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ተሳታፊዎች ሐሳብ የማቅረብ እድሉ እንደሚሰጣቸው የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 167(1) ይገልጻል። ይህንን ተከትሎም ተሳታፊዎች አስተያየት እና ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ አስረጂዎች/ባለሙያዎች በቀረቡ አስተያየቶች ላይ ሐሳብ ይሰጡበታል። ተከትሎም ኹለተኛ ዙር ጥያቄ እና አስተያየት ቀርቦ አስረጂ/ባለሙያዎች በድጋሚ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ የምክር ቤቱ ደንብ አስቀምጧል።
በተግባር ተሳታፊዎች ሥማቸውን እና የመጡበትን ቦታ ከገለጹ በኋላ ከአስረጂው ተጨማሪ ማብራሪያ ሊጠይቁ ወይም ሐሳባቸውን ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ያስረዳሉ። የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ መንበር አክለውም ስብሰባው በኹለቱም ወገን ለሚደረግ ውይይት ክፍት መሆኑ ይገልጻሉ። በጊዜ ምክንያት ሐሳቦች ሳይነሱ የሚተውበት አጋጣሚ አለመኖሩን የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሊቀ መናብርት ይገልጻሉ።
3. ሕዝባዊ ውይይቶች ለምን ያህል ጊዜ ይካሄዱ?
ሕዝባዊ ውይይቶች በአንድ ረቂቅ ሕግ ላይ በቂ ናቸው ተብሎ እስከሚታመንባቸው ብሎም በቂ ባለድርሻ አካላት እና የተለያዩ ዜጎች ተሳትፈውበታል ማለት እስከሚቻልበት ጊዜ ሊደረጉ ይገባል። በሕዝባዊ ውይይት ላይ የሚመጡ ተሳታፊዎች በጊዜ እጥረት ሐሳባቸውን ሳይገልጹ መመለስ አይገባቸውም። ነገር ግን ሕዝባዊ ውይይቶች ሕጎችን ከመውጣጥ ማጓተት፣ አላስፈላጊ መዘግየትም መፍጠር የለባቸውም። ኹለቱ መቻቻል አለባቸው።
በኢትዮጵያ ስላለው አሰራር የምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኀን ዳይሬክተር ሲያስረዱ ብዙውን ጊዜ ሕዝባዊ ውይይቶች የሚደረጉት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ሕጉ የተለየ ትኩረት የሚስብ ከሆነ ኹለተኛ ውይይት ሊዘጋጅ ይችላል። የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 167(3) ቋሚ ኮሚቴዎች ከባለሙያ፣ አስረጂም ሆነ ከሕዝብ ጋር የሚያደርጉት ውይይት እንደሁኔታው በተደጋጋሚ ሊደረግ እንደሚችል ይገልጻል። የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ውይይቶቹ ከአንድ ጊዜ በላይ፣ ለኹለት እና ሦስት ጊዜ ሊካሄዱ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ሲያስረዱ፤ የታሰበውን ያህል ቁጥር ተሳታፊ ካልተገኘ (የመጡትን በመበተን እና ሌላ በመጥራት)፣ የተጠበቁ ባለድርሻ አካላት ካልመጡ እና ኮሚቴው ያገኘው ግብዓት በቂ ነው ብሎ የማያምን ከሆነ እንደሆነ ይገልጻሉ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሳታፊዎች በማጣት ሕዝባዊ ውይይቶች በድጋሚ መጥራታቸው በተለያዩ ጊዜያት የሚሰሙ ዜናዎች ናቸው። ባለሙያዎች ብሎም የሲቪክ ተቋማት ሕጎች ከወጡ በኋላ ትችት ከማቅረብ ይልቅ በሕዝባዊ ውይይቶች ላይ የመሳተፍ ተነሳሽነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የአንድ ቋሞ ኮሜቴ ሊቀ መንበር ይመክራሉ።
ተደጋጋሚ ውይይቶችን ለማድረግ ሌላው ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው ረቂቅ ሕጎች ካላቸው ስፋት፣ አዲስነት እና በማኅበረሰቡ ላይ ከሚኖራቸው ውጤት አንጻር በቂ ግብዓት አልተገኘም የሚለው ሲሆን ይህንን በሚመለከት በቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መናብርት እና አባላት እውቀት እና ውሳኔ ላይ ብቻ ከሚመሰረት ይልቅ ወጥ የሆነ አሰራር የሚዘረጋበት አጋጣሚ ቢገኝ ተመራጭ ይሆናል።
4) አስተያየቶችን ለመቀበል ያለ ተነሳሽነት
ማኅበረሰቡ፣ የሲቪክ ተቋማትም ሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቋሚ ኮሚቴ በሚጠሩ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉት የሚሰጡዋቸው አስተያየቶች ግምት ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት ሲኖራቸው ነው። የፓርላማ ሕዝባዊ ውይይቶች የሚካሄዱት ለይስሙላ፣ ሒደቱ ቅቡልነት እንዲያገኝ ነው የሚሉ ችትቶች በየትኛው ሀገር ስርዓት ውስጥ ይነሳሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማኅበረሰቡ በሚደረጉ ጥሪዎች ላይ ላለመገኘቱ እና ለመሳተፍ ተነሳሽነት የሌለው በዋነኛነት አስተያየቱ ግምት ውስጥ ይገባል የሚል እምነት ስለሌለው መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት እና የምክር ቤቱ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ይስማማሉ።
በምክር ቤቱ በሚካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ውስጥ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ብሎም ረቂቅ ሕጎቹን የሚያመጡት ተቋማት የተሳታፊዎች አስተያየቶችን ምን ያክል ግምት ውስጥ ይከታሉ የሚለው አጠያያቂ ነው። ለዚህ ዋነኛ መገለጫው ደግሞ የምክር ቤቱ መቀመጫዎች እና የመንግሥት መዋቅር በአንድ የፖለቲካ ግንባር – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዲግ) – እና እህት ድርጅቶቹ ቁጥጥር ውስጥ መቆየቱ መሆኑ ነው።
ፓርቲው በባህሪው የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጅ ነበር። ለዚህም ዋነኛው መገለጫው ያለው የውስጥ ዲሞክራሲ (Centralized Democracy) እና የፓርቲ ዲሲፕሊን ነበር። ይህም ማለት በፓርቲ ውስጥ በሚኖር የውስጥ ወይይት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ፣ የፓርቲ አባል እና የምክር ቤት አባል በሆኑ ግለሰቦች ሊተች፣ ተቃራኒ አቋም ሊያዝበትም አይችልም። በዚህም ምክንያት የፓርቲው አባላት የሆኑ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አባላት ፓርቲያቸው የመሠረተው መንግሥት የሚያመነጯቸውን ሕጎች የመተቸት አዝማሚያ አያሳዩም። በሕዝባዊ ውይይት ጊዜ የሚቀርቡ ሐሳቦች ከሕግ አመንጪው የተለዩ ከሆኑ የቋሚ ኮሚቴዎቹ እንዳይቀበሉ የፓርቲያቸው አካሄድ አይፍቅድም። በዚህም ምክንያት የምክር ቤቱ አባላት ተጠያቂነታቸው ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው ‹‹ለሕዝቡ፣ ለሕገ መንግሥቱ እና ለሕሊናቸው ነው ወይስ ለፓርቲያቸው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ኖረዋል።
የአንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የፓርቲው አካሄድ የምክር ቤቱ አባላት እንደ ግለሰብ አቋም እንዳይዙ ያደርጋቸው እንደነበር አይሸሽጉም። እንደ ቋሚ ኮሚቴዋ ሊቀ መንበር አገላለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ እና ኢሕአዲግ’ን አፍርሰው የብልጽግና ፓርቲን ከመሰረቱ በኋላ ይሄ እንደተለወጠ እና በረቂቅ አዋጆች ላይ የጠለቀ ውይይት እንደሚደረግ፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ላይ የሚነሱ ሐሳቦችም እንደሚካተቱ ይገልጻሉ። አክለውም ረቂቅ ሕግ ከሚያቀርቡ ተቋማት ለሚመጡ አስረጂዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች እንደሚቀርብላቸው እና ረቂቅ ሕጎች ከመጽደቃቸው በፊት እንደሚሻሻሉም ይገልጻሉ።
5) እውቅና እና ማበረታቻ
ተጠያቂነት ሊሰፍን የሚችለው ብሎም ተሳታፊዎች እምነት የሚያድርባቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የቱን አስተያየት ግምት ውስጥ እንደከተቱ እና እንደተዉ፣ ከምክንያት ጋር ለተሳታፊዎች ሲያሳውቁ ነው። አስተያየት ሰጪዎች ሐሳባቸውን ብቻ ገልጸው መቅረት አይኖርባቸውም። በየነጥብ ተለይቶ ማድረግ ባይቻልም ጠቅለል ተደርጎ ግምት ውስጥ የገቡ እና ያልገቡ አስተያየቶች ለተሳታፊው ሊነገሩ ይችላሉ። ጊዜው በቂ ከሆነ ሕዝባዊ ውይይቶቹ በተካሄዱበት መድረክ ወይም ሌላ መድረክ ተጠርቶ ሊደረግ ይችላል። ይሄ በተሳታፊዎች እምነት እንዲያድር ብቻ ሳይሆን፣ በተሳፊዎች እና ሕዝባዊ ውይይት በሚያዘጋጁት ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል ያለው ትብብር እንዲጠነክርም ምክንያት ይሆናል። በሕዝብ ተወካዎች ምክር ቤት ባለው ልምድ ግን ይህን የማድረግ አካሄድ የለም። ሐሳቦች ከቀረቡ በኋላ ይመዘገባሉ እንጂ ተቀባይነት ማግኘቱ ወይም አለማግኘቱ አይገለጽም።
ሌላው በተደጋጋሚ ተሳታፊ ለሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማት እውቅና እና ማበረታቻ መስጠት ነው። ይህ ግለሰቦች እና ተቋማቱ በድጋሚ ተሳትፎ እንዲያደጉ ያበረታታል። የአንድ ቋሚ ኮሚቴ አባል ግን ለሀገር በተለያዩ ዘርፎች ላይ አስተዋጽዖ ላደረጉ እንጂ በሕጎች የማውጣጥ ሒደት ውስጥ አበርከቷቸው ጎልቶ ለሚታዩ ግለሰቦች ማበረታቻ የሚሰጥበት አጋጣሚ አለመኖሩን ይገልጻሉ። የሌላ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበርም በተመሳሳይ ሐሳቡን እንደ አማራጭ ወስደውት እንደማያውቁ፣ ነገር ግን ጥሩ አካሄድ በመሆኑ ለወደፊቱ ምክረ ሐሳቡን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013



