ፍጻሜው እንዲያምር ሰላማዊ ፉክክሩ ይለምልም

0
534

በኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ብቅ እያሉ ሰላማዊ አካሔድን ‹ከሚያደናቅፉት› መካከል ዋነኛው የዴሞክራሲ ስርዓት አስተዳደር መለያ የሆነው የምርጫ ጉዳይ ነው። በዚህ የምርጫ ሂደት ላይ ታዲያ ባለፉት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ደግሞ በኢሕአዴግ ዘመን የተደረጉት ምርጫዎች አንዳቸውም መልካምና ሰላማዊ ፍጻሜ አልነበራቸውም ለማለት የሚያስደፍርበት ጊዜ መኖሩን መናገር ይቻላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ሰዎች ባልታሰበ እና ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ ወደ ሰዋራ እስር ቤት ተወስደዋል፣ ሰብዓዊ መብታቸው ተረግጦ ተደብድበዋል፣ በኋላም ለሕልፈትም ተዳርገዋል።

ጠባሳው ዘመናትን ተሻግሮ እንኳን የማይሽረው በምርጫ እና ምርጫን ተከትሎ የተከሰቱት መራር ገጠመኞች ዛሬም ድረስ ሕዝብ ምርጫን በአሉታዊ ጎኑ እንዲመለከተው ያደረጉ ናቸው። ምርጫ ማለት ልጅን ከወላጅ ጉያ የሚነጥቅ ጨካኝ የጊዜ ዑደት የሚያመጣው እንጂ ሰዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ መብታቸው ተጠቅመው ድምጻቸውን የሚሰጡበት እና የሥልጣን ባለቤት መሆናቸው የሚረጋገጥበት እንዳልሆነ ከተገነዘቡት ቆይተዋል። ምርጫንም ከልባቸው ለማውጣት የተቃረቡ ለመኖራቸው አያጠራጥርም። ከዚህ ቀደም በተደረጉት አምስት ምርጫዎች ላይ ሰዎች ያልታሰሩበት፣ ያልተደበደቡበት እና ያልተገደሉበት ምርጫን ማግኘት ይከብዳል እስኪባል ድረስ፣ ፍጻሜያቸው እጅግ አሳዛኝ ምርጫዎች ለመካሔዳቸው ሕያው ምስክሮች በርካታ ናቸው።

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በየጊዜው ቀን ቆጥሮ በሚደረጉ ምርጫዎች ሁሉ ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሁም ፍትሀዊ ምርጫዎችን አካሂዳለሁ በሚል ቃል እየገባ እና ምሎ እየተገዘተ በሚያሰናዳው ምርጫ ሁሉ ካለፈው በባሰ እንጂ በተሻለ መንገድ ሲያስፈጽም አልታየም። እናም የአዙሪቱ ማብቂያ እና በሕዝብ ድምጽ ላይ ያለው ቀልድ ማቆሚያው መቼ እንደሚሆን በጥያቄዎች የተሞሉ ጊዜያት በርካታ ናቸው። ምላሻቸውም ሰማይ ያህል የራቀ ነገር ግን ደግሞ በእጅጉ ቀላል እንደሆነም ይታመናል።

በጎረቤት የአፍሪካ አገራት የሚታዩ ተመሳሳይ ችግሮች ደግሞ በምዕራባውያን እና ከውጭ ሆነው በሚታዘቡ አካላት ዘንድ ይህ ችግሩ አኅጉር ዐቀፍ ይሆንን ብሎ እስከ መጠየቅ የተደረሰበት እንደሆነም የሚታወቅ ሀቅ ነው። በእርግጥ ደግሞ በአፍሪካም ውስጥ ሆነው እጅግ ሥልጣኔ የተሞላበት እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የተካሔደባቸው አገራት መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም። ሆኖም ግን ከአኅጉሩ የአገራት ቁጥር አንጻር እዚህ ግባ የማይባል ቁጥር በመኖሩ ችግሩን በደምሳሳው አኅጉራዊ አድርጎ ለማሰብ ይገፋናል።

በአሁኑ ወቅት የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ እና አሮጌው አቁማዳ ወጥቶ አዲስ አቁማዳው አዲስ ወይን ጠጅ ይዞ ይገኛል የሚባልባት ኢትዮጵያ፣ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሔድ ሽር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች። ይህ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች የሚለይባቸው ምክንያቶች ቢኖሩም የሚመሳሰልባቸው ነገሮች እንዳሉት ደግሞ መናገርም ይቻላል።

ጅማሬው እና እስከ አሁን ድረስ ያለው እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ የሚከወን እና የምርጫ ቅስቀሳ ጅማሬዎች በእጅጉ ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ እናንሳ፤ በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት አገሪቱ አይታው የማታውቀው እና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ በአንጻራዊነት ሰላማዊ የተባለ የምርጫ ቅስቀሳ እና ክርክር መካሔዱ የሚታወስ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ሕዝብ በእርግጥም የተባለው ተስፋ ሊከናወን መንገድ ላይ መሆኑን በመገመት ትልቅ ተስፋ ሰንቆ ነበር፤ የምርጫውን ሒደት እና ውጤት ሲጠባበቅ የነበረው።

ነገር ግን ፍጻሜው የሕዝብን ድምጽ ያላከበረ እና የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ አሳዛኝ ነበር። ይህ የ1997 ምርጫ እስከ ዛሬም ድረስ ትውልድ የምርጫ ሐሳብ ሲኖረው የሚያስታውሰው ከባድ ጠባሳ መሆኑም ይታወቃል።
በመሆኑም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የተጀመረው ሰላማዊ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ፍጻሜያቸውም እንዲያምር አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ጅማሬያቸው እምብዛም የማይታማው እና ፍጹም ሰላማዊ የሚመስሉት ምርጫዎች ፍጻሜያቸው አስደሳች ሳይሆን በተቃራኒው ሆነው የሚገኙ በመሆናቸው፣ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው ይገባል።

ባሳለፍነው ሳምንት በርካታ ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው የምርጫ ቅስቀሳቸውን የጀመሩት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ችግር እና እንከን ቅስቀሳ ማካሔዳቸውን እና ተመራርቀው ለመለያየት መቻላቸውን መታዘብ ልብን የሚሞላ ጉዳይ ነው። ይህም ታዲያ በምርጫ ሒደቱም ላይ ቀጥሎ እድለኛ አሸናፊ እና ሰላማዊ ተሸናፊዎችን መፍጠር የሚቻልበት እንዲሆን ሁሉም አካል አጽንኦት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

እየተፈጠሩ ያሉ ተቋማትን እና ያላቸውን አቋም በተወሰነ መልኩ ማድነቅ የሚቻል ሲሆን፤ ተጠናክሮ ቀጥሎ አገርን ለመገንባት የሚኖረው ሚና በጉልህ እንዲጻፍ አዲስ ማለዳ ከወዲሁ ልብ ይባል ትላለች። ይህ ብቻም ሳይሆን ከመንግሥት እና ከገዢው ፓርቲ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫናም በእምቢተኝነት ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ ማለዳ አቋም ነው። ያለፉት ዘመናት ላይ የሕዝብን ልብ ዝቅ ያደረጉ እና መጥፎ ስሜትን ሲፈጥሩ የነበሩ ምርጫዎችን ማስተካከያው እና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጫ ጊዜው አሁን እንደሆነ በመገንዘብ የትኛውም የምርጫ ሒደት ላይ ተሳታፊው ሁሉ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ እና እንዲያስፈጽም ግድ ይላል። በፍትሐዊ አካሄዶች ላይ የተጀመረው ስድስተኛው ምርጫ በአስፈጻሚ አካላትም ዘንድ ነጻ እና ፍትሀዊ ሆኖ እንደተጀመረ እንዲጠናቀቅ በተገቢው መንገድ ሊመራም ይገባል።

ባለፉት ጊዜያት የነበሩት ምርጫዎች በተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በገዢው ፓርቲ አለመግባባት ወይም ደግሞ አለመተማመን ብቻ የተመሰረቱ ግጭቶች ሳይሆኑ የአስፈጻሚው አካልም ገለልተኛነት እና ከጫና ነጻ መሆን ጋር የተያያዙ ችግሮች የአዙሪቱን ጥንካሬ ለማስቀጠል አይነተኛ ሁኔታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ይህን አዙሪት በመስበር እና የተጀመረውን ልብን የሚያሞቅ እንቅስቃሴ ከወዲሁ በማጠናከር እና በጠንካራ ክትትል በማስፈጸም ታሪካዊ አደራውን በአገራዊ ስሜት እንዲወጣ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ማንም ቢያሸንፍ ከዚህ በኋላ በሕዝብ ደረጃ ምርጫ ሲባል የሚፈራ፣ ተስፋ የሚቆረጥበት እና የማይፈለግ ሳይሆን፤ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መንገድ፣ ሕዝብ የሚወደውን እና የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ ይሆነኛል ይመጥነኛል፣ ይመራኛል የሚለውን ሐሳብ የሚያስተጋባበት እና እያንዳንዱ ሰው ድምጽ በሚሰጥበት ወቅት በድምጹ ለውጥ የሚመጣ ሆኖ እንዲሰማው ማድረግ ይገባል ስትልም አዲስ ማለዳ ሐሳቧን ታስተጋባለች። የተጀመረው የሰላማዊ አካሔድ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ እስከ ምርጫው ቀን አልፎም እስከ መጨረሻው እንዲዘልቅ እና ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ አዲስ ማለዳ ትመኛለች፤ አቋሟንም ታስተጋባለች።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here