በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርተ(ቦዴፓ) በክልሉ ያሉት ጽሕፈት ቤቶቹ እንደተዘጉበት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዮሐንስ ተሰማ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት በክልሉ አማራጭ ሀሳብ አቅርበን በሙሉ አቅም በምርጫ እንዳንወዳደር የክልሉ መንግሥት ፓርቲው ያሉትን ሙሉ ጽሕፈት ቤቶች ዘግቶ እስካሁንም ድረስ እንዳልተከፈተላቸው ተናግረዋል።ፓርቲው በሚቀጥለው ስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፍ ለማስተጓጎል የክልሉ መንግሥት የፓርቲውን አመራሮችና አባላት በሀሰት በመወንጀል ለእስር እንደዳረጋቸው ዩሐንስ ገለጸዋል።
የፓርቲው አመራሮች በክልሉ መንግሥት ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ቆይተው ባሳለፍነው የካቲት 19/2013 መለቀቃቸውን ዮሐንስ አስታውሰዋል። ለሰባት ወራት በእሰር ቆይተው የተቀቁት የፓርቲው ሊቀመንብር አመንቴ ገሺ እና ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት እራሳቸው ዩሐንስ ተሰማ ናቸው። የፓርቲው ኹለት ከፍተኛ አመራሮች ከእስር ቢፈቱም ሌሎች የፓርቲው ስራ አስፈጻሚዎችና አባላት እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዩሐንስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የፓርቲው አመራሮች በእስር ላይ መቆየት፣ፓርቲው ያሉት 12 ጽሕፈት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው እና የታሰሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና አባልት አስካሁን ድረስ አለመፈታታችው የፊታችን ግንቦት 28/2013 ለሚካሄደው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እንዳይሰራ አድርጎታል ነው የተባለው። በዚህም የፓርቲው አመራሮች እና አባላቶች በእስር ላይ እያሉ የተጀመረው የእጩዎች ምዝገባ የፓርቲው ከፍተኛ ኹለት አመራሮች እስከተፈቱበት ስዓት ድረስ አለመጀመሩን ያስታወሱት ዮሐንስ በተቻላቸው መጠን ኹለቱ አመራሮች እጩዎችን ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አክለው ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት በፓርቲው ላይ ጫና እያሳደረ ቢሆንም ፓርቲው ያለበትን ጫና ተቋቁሞ በሚቀጥለው ጠቅላላ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያረጋገጡት ዮሐንስ፣ ፓርቲው የዘገየባቸውን ሥራዎች ለመከወን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል። በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚዎችና አባላትን ያሰራቸው የክልሉ መነግሥት ከለእስር አንድለቃቸውና በምርጫ እንድሳተፉ ፓርቲው አሳስቧል።
የፓርቲው ኹለት ከፍተኛ አመራሮች ከእስር የተለቀቁት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ እና በመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ትብብር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ዮሐንስ የምርጫ ተሳትፏችን ጠንካራ እንዲሆን አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ትብብር ያስፈልገናል ብለዋል። የአመራሮቹ መታሰር ፓርቲዉ በመጪዉ ግንቦት ማብቂያ ሊደረግ በታቀደዉ ምርጫ ለመሳተፍ በሚያደርገዉ ዝግጅት ላይ ተፅዕኖ ማሰዳሩን በተደጋጋሚ ሲያስታዉቅ ነበር።
የፓርቲው አመራሮች ገና ፓርቲውን ለመመስረት በዝግጅት ላይ እያሉ አስር አመራሮች በክልሉ መንግስት መታሰራቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚተወስ ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን እንዳስቆም በደብዳቤ ማሳወቃቸውንም አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው።
የክልሉ መንግሥት በበኩሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ባለስልጣናት የሚታሰሩት በክልሉ በነበሩት ግጭቶች በመሳተፍ ተጠርጥረዉ እንደሆነ መግለጹ የሚታወስ ነው። የክልሉ መንግሥት ይህን ይበል እንጅ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በተፎካካሪነት እንዳይቀርቡ ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸው ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ከእሥር የተለቀቁት የፓርቲው አመራሮች በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ አቃቢ ሕግ ጥረት ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥት በወንጀል ተጠርጥረው ስለታሰሩ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም ሲል አመራሮቹ ከእስር በተለቀቁበት ጊዜ መናገሩ የሚታወስ ነው።
አዲስ ማለዳ የፓርቲውን ጽሕፈት ቤት መዘጋትና የታሰሩ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚዎችና አባልት እስር በዚህ የምርጫ ወቅት እንደት እንደሚየው ምላሽ ለማግኘት ለክልሉ መንግስት የኮሙኑኬሽን ኃላፊ መለስ በየነ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ሊመልሱ አልቻሉም።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013



