በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አራት ቅርንጫፍ ፅህፈትቤቶች ለሠራተኞች እንዲሁም ወደየ ቅርንጫፎቹ አገልግሎት ለማግኘት ለሚሄዱ ተገልጋዮች ምቹ ባለመለሆናቸው የተነሳ ሰራተኞች በተደጋጋሚ ለጤና ዕክል እንደሚዳረጉ ታወቀ።
የንፋስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፣የየካ ክፍለ ከተማ እንዲሁም የቦሌ እና የኮልፌ ክፍለ ከተማ የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ፅህፈትቤቶች በቦታ ጥበት እና ለሥራ እንቅስቃሴ ምቹ ባለመሆናቸው ምክንያት ሰራተኞች ለተለያዩ የጤና ዕክል መዳረጋቸው አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሠተኞችም ሆነ ከተገልጋዮች በየጊዜው ቅሬታ እየቀረበ እንደሚገኝ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ፍሬው ተሻለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አክለውም በተለይ የየካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈትቤት ከሁሉም ቅርንጫፎች በተለየ ችግሮች እንዳሉበት ባለስልጣኑ እንደሚያውቅ እና ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ያለ ሥራ እንዳለም ተናግረዋል። የኮልፌ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈትቤትደግሞ የሚሠሩበት ቦታ የክፍለ ከተማው ቢሮ የሚገኝበት ሕንፃ ምድር ቤት ወይንም ‘ቤዝመንት’ ላይ በመሆኑ ቦታው ለሥራ ምቹ አይደለም በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ ምክንያት ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየተጋለጥን ነው በማለት ከሠራተኞቹ ቅሬታ እንደሚደርሳቸውም ዳይሬክተር ፍሬው ተሻለ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እና ወደ አሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ለተለያዩ ግልጋሎት እንደሚመላለሱ የገለጹት አሽከርካሪ ትንሳዔ ቀለሙ የግል መኪኖች ስላሏቸው ለመሸጥ ሆነ በሚገዙበት ወቅት ስም ለመዘዋወር በተለይ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ወደ የካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈትቤቶች በሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ግልጋሎት ለማግኘት ቦታዎቹ ጠባብ በመሆናቸው ምክንያት መጉላላት እና በቶሎ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ ተናግረዋል አክውም እነዚህ ተቋማት ሰዎች በየቀኑ የሚመላለሱባቸው በመሆናቸው እና አሁን ከፍተኛ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ያለበት ወቅት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ዓላማና ተፈጻሚነት አንቀጽ ቁጥር 52 (ለ) የሥራ ቦታን ለመንግሥት ሠራተኞች ደህንነትና ጤንነት በሚስማማ መልኩ ማዘጋጀት፣ ማሻሻልና መጠበቅ እና (ሐ) የመንግሥት መሥሪያ ቤት በጐ በሆነ ማህበራዊ ሕይወት ላይ ተመሥርቶ አመርቂ የሥራ ውጤት እንዲያስመዘግብ ማብቃት ይሆናል በማለት አስቀምጧል።
አንቀጽ ቁጥር 53 (1) ላይ ደግሞ በሥራ ላይ ስለሚደርስ ጉዳት “በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት” ማለት በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም በሥራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው በማት ይገልጻል። (2) “በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ” ማለት ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛው መደበኛ ሥራውን በማከናወን ላይ እንዳለ ወይም ከሥራው ጋር በተያያዘ ምክንያት በአካሉ ወይም በአካሉ የተፈጥሮ ተግባር ላይ በድንገት የሚደርስ ጉዳት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሠራተኛው ከመደበኛ ሥራው፣የሥራ ቦታው ወይም የሥራ ሰዓቱ ውጭ ሥልጣኑ በሚፈቅድለት ሰው የተሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ላይ እያለ የደረሰን ጉዳት ካለ በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ እንደሆነ ይቆጠራል ተብሎ ይተረጎማል ሲሉ የሕግ ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት ዮሐንስ ግርማ ገልጸዋል።
አንቀጽ ቁጥር 53 (2) ላይ ሠራተኛው በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የደረሰን ድንገተኛ አደጋ ወይም ጥፋት ለመከላከል በሥራ ሰዓት ወይም ከሥራ ሰዓት ውጭ በሚፈጽመው ተግባር ምክንያት የደረሰን ጉዳት፣ ለሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት ወይም መሥሪያ ቤቱ ለዚህ ተግባር በተከራየውና በግልጽ በመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት በመጓዝ ላይ በነበረበት ጊዜ የደረሰን ጉዳት እና ስሌሎች የሥራ ላይ ስለሚደርሱ ጉዳቶች በግልጽ አስቀምጧል።
የሕግ ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት ዮሐንስ አሠሪ ተቋማት ምቹ የሆነ የሥራ ቦታ ከሌላቸው ሌላ ቢሮ ማዘጋጀት አለባቸው ተቋማቱ ይህንን ካላደረጉ እና በሠራተኞቻቸው ላይ ጉዳት መድረሱ በሕክምና ከተረጋገጠ ተጠያቂ ይሆናሉ በማለት ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013



