በደብረ ብርሃን ከተማ ዓለም ዐቀፍ ሆስፒታል በግል ባለሀብቶች ሊገነባ ነው

0
1011

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በግል ባለሀብቶች ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚሟላ ሆስፒታል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በሰሜን ሽዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን ላይ የሚገነባው ዓለም ዓቀፍ ሆስፒታል “ኢስተርን ስታር ተርሸሪ ሆስፒታል አክሲዎን ማኅበር” የተባለ ስያሜ እንደተሰጠው አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው ኢስተርን ስታር ተርሸሪ ሆስፒታል በ5.5 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው ተብሏል፡፡ የሆስፐታሉ ግንባታ የመጀመሪያ ክፍል ሥራ በአሁኑ ጊዜ በመሰራት ላይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ለሆስፖታሉ ግንባታ ኹለት ነጥብ አምስት(2.5) ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ጸሐየ ገብረህይወት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ጸሐየ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የሚታየውን የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ተቋም ለማቋቋም አክሲዮን አደራጆቹ ከአምስት ዓመት በላይ ከፍተኛ ጥረት ሲደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በግል ባለሀብቶች ደብረ ብርሃን ላይ የሚገነባው ተሪሸሪ ሆስፒታል በኢትዮጵያ የሚታየውን ደረጃውን የጠበቀ ከፍተኛ የህክምና ተቋም እጥረት ከመሸፈን በውጭ አገር የሚሰጡ ሕክምናዎችን በመስጠት የሕሙማን ሕይወት እንደሚታደግ ተመላክቷል፡፡ ለዚህም ምስረታውን ከማደራጀት ጀምሮ በርካታ የሕክመና ባለሙያዎች እንዳሉ የጠቆሙት ጸሐዬ በውጭ አገር የሚያገለግሉ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለማኅበረሰቡ እንዲያገለግሉ እድል የሚሰጥ ሆስፒታል እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የሆስፒታሉ አደራጆች ዋነኛ አላማ በውጭ አገር የሚሰጡ ህክምናዎችን በአገር ውስጥ በመስጠት የታካሚዎችን ሕይወት መታደግና ከተጋነነ የሕክምና ወጭ መታደግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ከዚህ በተጫማሪም ሆስፒታሉ ከሚገኘው ትርፍ አስርር በመቶ የሚሆነውን አቅም ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ከወዲሁ መወሰኑን ጸሐዬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

የኢስተርን ስታር ተርሸሪ ሆስፒታል አክሲዮን ማኅበር የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት ሆስፒታሉን ገንብቶ ሥራ ማስጀመር መሆኑን የጠቆሙት ጸሐዬ፣ በሂደት የሕክምና ቁሳቁስና መድሐኒት ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት፣ የሕክምና ትምህርት ማዕከል መገንባትና የሕክምና ምርምር ማዕከል ማቋቋም በመሥራት ዘርፉን የማዘመን ሥራ ወደፊት እንደሚሰራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አደራጆቹ ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ተሪሽሪ ሆስፒታሉ የሚገነባበት ቦታ በማፈላለግ እንደሆነ ያስታወሱት ጸሐዬ፣ አሁን ላይ ለሆስፒታል ግንባታ የሚሆን ቦታ የአማራ ክልልና ሰሜን ሽዋ ዞን በጋራ ትብብር በደብረ ብርሃን ከተማ ቦታ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ጸሐዬ እንደሚሉት ተሪሽሪ ሆስፒታሉን ለመገንባት በአዲስ አበባ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቢቆዩም ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል እና ሰሜን ሽዋ ዞን በከፍተኛ አቀባበል ያለ ምንም እንግልት የመሥሪያ ቦታ እንደፈቀዱላቸው በመግለጽ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቅድመ ዝግጅቱ አካል የሆነው አክሲዮን ሽያጭ ሲሆን፣ ይህም በሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች አክሲዮን እየተሸጠ መሆኑን የአደራጆች ቦርድ አመራሮች ገልፀዋል፡፡
የአንድ አክሲዎን ዋጋ አንድ ሽሕ ብር ሲሆን አንድ ባለአክሲዎን ዝቅተኛ መግዛት የሚችለው 20 አክሲዎን ማለትም 20 ሺሕ ብር ሲሆን አንድ ባለአክሲዎን ከፍተኛ መግዛት የሚችለው የአክሲዎን ዋጋ 25 ሚሊዮን ብር ነው ተብሏል፡፡
የሆስፒታል ግንባታው ለግንባታ ከሚያስፈልገው ገንዘብ 25 በመቶው ከተሰበሰበ የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የኢንቨስትመንት ሕጉ ለባለሀብቶች የሚሰጠው የኢንቨስትመንት መሬት በኹለት ዓመት ውስጥ ግንባት ወይም ወደ ስራ ካልተገባ ካልጀመረ ቦታወን እንደሚነጥቅ ይደነግጋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ አዲስ ለመገንባት የታቀደው ተርሸሪ ሆስፒታል በአስቸኳይ አክስዮን ሽያጩን በማሳለጥ ወደ ስራ እንደሚገባም ተጠብቋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here