ግዮን ሆቴል አሁን ባለበት ይዞታ እንደማይሸጥ ተገለጸ

0
1086

ግዮን ሆቴልን በተለያየ ጊዜ ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የታቀደ ቢሆንም ሆቴሉ መልሶ የማልማት ሥራ ከተሠራበት በኋላ ወደ ግል ይዞታ እንደሚዛወር የመሬት ባንክ እና የልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ግዮን ሆቴልን በምን መንገድ ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወር ቢደረግ ያዋጣል የሚለውን ተጠንቶ እና በቦታው ላይ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ፣ ወደ ግል ይዞታ ብናዘዋውረው ትርፋማ እንሆናለን በሚለው ሐሳብ ስምምነት ላይ መደረሱን ከኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢንተርፕራይዝ የግዮን ሆቴልን ወደ ግል ለማዞር በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል። በተያያዘም የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል እንደ ግዮን ሁሉ ወደ ግል ለማዞር ታስቦ እንደነበር አይዘነጋም።

<ለሸገር አዲስ ገጽታ> የሚል ሥያሜ የተሰጠው የተለያዩ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ይዞታዎችን ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ላይ የማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፣ ለይዞታዎቹ አዲስ፣ ውብ እና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሐሳብ ለማቅረብ በፕሮጀክት መልክ ተቀርፆ እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም ሁሉንም የኅብረተሰብን ክፍል የሚያቅፍ ውድድር በመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን እየተሠራ እንደሆነ ተጠቅሷል። ግዮን ሆቴልም አንዱ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው። በተለያዩ ቦታች በሚገኙ የመንግሥት ይዞታዎች በሆኑ ቦታች ባለ ሰባ ከኮብ ሆቴሎች የመገንባ ዕቅድ እንዳለውም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

ቁጥራቸው በርከት ያለ የመንግሥት ተቋማት ይገኙባቸዋል የተባሉ አምስት መዳረሻዎችን ለማልማት በተያዘው የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን ዕቅድ ላይ ከተቀመጡ አምስት መዳረሻዎች መካከል ይህ የጊዮን ሆቴልን የተመለከተው ሥራም አንዱ መሆኑን ሌንሳ ገልጸዋል።
አያይዘውም ፕሮጀክቶቹን የዘረዘሩ ሲሆን፣ የመጀመርያው መዳረሻ ቦሌ ሲቪል አቪዬሽንን ያካትታል፣ ኹለተኛው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚገኝበት በተለምዶ ደምበል አካባቢን ይይዛል ብለዋል። እንዲሁም ሦስተኛው እና በስፋቱ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለት የግዮን ሆቴል መዳረሻ እና አራት ኪሎ የሚገኘው የትምህርት ሚኒስቴር በአራተኛ መዳረሻነት ተይዟል። የመጨረሻው እና አምስተኛው መዳረሻ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የፕላንና ልማት ኮሚሽንን እንደሚያካልል ተገልጿል።
በ1941 ተቋቁሞ የሆቴል አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግዮን ሆቴል በመንግሥት የልማት ድርጅት ስር ይተዳደራል። በውስጡም ከ397 በላይ ቋሚ ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድር መረጃዎች ያሳያሉ።

የገንዘብ ሚስቴር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ብሩክ ታየ (ዶ/ር) ንብረትን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር (ፕራይቬታይዜሽን) በአራት መንገዶች እንደሚፈጸም ገልጸዋል። ከእነዚህም አንዱ መንግሥት የቀደመ ይዞታውን ወይም የሞኖፖል ሚናውን መተው ሲፈልግ የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍበት መንገድ ነው በማለት በቀዳሚነት አስረድተዋል።

መንግሥት በትምህርት መስክ የነበረውን ብቸኛ ሚና ለግሉ ክፍት በማድረግ የወሰደውን ዕርምጃ የጠቀሱት ብሩክ፣ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር መንግሥት አሁን የመረጠውና እንግሊዝም ከ40 ዓመታት በፊት የተገበረችው ነው ብለዋል። ነገር ግን ውጤቱ ጥሩ እንዳልነበረ አስታውሰው ገልጸዋል።

ሌላው አማራጭ የመንግሥት ድርጅቶችን በኮንትራት ማኔጅመንት ለግል ድርጅቶች መስጠት ሲሆን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ባለቤትነትን ሳያስነካ ማካሄድ እንደሚቻል አስታውቀዋል።
የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስር የሚገኙ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎችን የቢዝነስ ሐሳብ ካላቸው ሰዎች ጋር በጋራ ለማልማት ማቀዱ ይታወሳል። ግዮን ሆቴልን በሚመለከት ያሉ የተለያዩ እድሳትና የተጨማሪ ሕንጻ ግንባታ ሥራዎችም የዚህ እቅድ አካል ናቸው።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here