ከዓለም ዐቀፍ የጥራት አረጋጋጭ አካል (SGS) የሦስተኛ ወገን የጥራት ሰርተፍኬት ባለማምጣታቸው አራት መቶ ሰባ ስድስት የሚሆኑ የውሃ መሳቢያዎች ወደ መጡበት አገር ተመላሽ እንዲሆኑ መደረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
መንግሥት የግብርና ምርቶች ከግብር ነፃ እንዲገቡ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በርከት ያሉ አስመጪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገቢና ወጪ እቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር እያሱ ስምኦን እንደተናገሩት ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ገቢ እቃዎች ውስጥ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የውሃ መሳቢያዎች እንደሚገኙበት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ምርቶቹ የኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ ቢወጣላቸውም ላለፉት ዓመታት በአገር ውስጥ በቤተ ሙከራ የመፈተሽ አቅም ባለመኖሩ በአርሶ አደሩ ላይ ይፈጠር የነበረውን የጥራት ጉድለት ችግሮችን ለመቅረፍ ሲባል ምርቶቹ የሦስተኛ ወገን የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ሲቀርብባቸው አስፈላጊው የጥራት ቁጥጥር ተደርጎበት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ላይ አራት መቶ ሰባ ስድስት የሚሆኑ የውሀ መሳቢያዎች ወደ መጡበት አገር ተመላሽ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።
በዋናነት ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በብሄራዊ ባንክ በኩል የሚያስገቡት ጋር ሳይሆን በዲያስፖራ አካውንት የሚጠቀሙት ባለሀብቶች ጋር እንደሆነ አክለው ተናግረዋል።
እንደ እያሱ ገለፃ ለአስመጪዎቹ በድረገፅ እንዲሁም በብሄራዊ ባንክ በኩል ማረጋገጫው እንደሚያፈልግ ማስታወቃቸውን ጠቅሰው ተመላሽ እንዲሆኑ የተደረጉባቸው ባለሀብቶች መረጃው እንደሌላቸው ሲናገሩ ነበር ብለዋል።
ነገር ግን እነኚህን የውሃ መሳቢያዎች ያለ ማረጋገጫ ሰርተፍኬታቸው ማስገባት እንደ አገር ገበሬው ላይ ጫና ይፈጥራል ብቃቱ ካልተረጋገጠ በትክክል መስራቱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም ሲሉ ጠቁመዋል።
አምስት የሚሆኑ አስመጪዎች ያስመጡዋቸው እነዚህ ውሃ መሳቢዎች መመለሳቸው እንደ አገርም ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ይከተናል ብለዋል። ምርቶቹን ለማስገባት የሚወጣው የውጪ ምንዛሬ ከፍተኛ ነው በዚህም እነዚህ ምርቶች ተመላሽ ሲደረጉ ኪሳራ ውስጥ እንገባለን ብለዋል። በአምስቱ አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ የጥራት ማረጋገጫ ሳይዙ የገቡ የውሃ መሳቢያዎች በዋናነት ወደ መጡባቸው አገራት ቻይና ፣ ዱባይ እና ህንድ እንዲመለሱ መደረጉም ታውቋል።
እንዲሁም ይህ ችግር የተፈጠረው መንግስት ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የውሃ ፓምፖችን ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ከመፍቀዱ ጋር ተያይዞ ምርቱ በስፋት መግባት መጀመሩን እና በአስመጪነትም በርካታ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ እየተሳተፉ መሆኑን ተከትሎ አንዳንድ በዘርፉ አስመጪነት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ይህንን የጥራት ሰርተፍኬት ባለማቅረባቸው ማስገባት እንደሆነም ዳይሬክተሩ አክለው አስታውቀዋል።
ከሶሶተኛ ወገን የጥራት ሰርተፍኬት አሰራር ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በደብዳቤ አሳውቀናል ያሉት ዳይሬክተሩ በተለይም የዳያስፖራ አካውንት ተጠቅመው ምርቶቹን የሚያስገቡ ባለሃብቶች ላይ ችግሩ በስፋት ስለሚስተዋል አስመጪዎች ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት አስፈላጊ ሰነዶችን አሟልተው መቅረብ እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ታህሳስ አራት 2012 አመት የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ከፍተኛ አመራሮች ፣ ዳይሬክተሮች እንዲሁም የግል ባለሀብቶች በተገኙበት የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መወሰኑ ይታወሳል፤ ይህም የሆነው የግብርና ሜካናይዜሽን ተደራሽነት ከፍ በማድረግ ለግብርናው ሁለንተናዊ እድገት እንደሚያሳድር ታምኖበት ነው።
በዚህም በዓይነት 624 ያህል የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ከታክስ ነጻ መደረጋቸውን ከእነዚህም መሳሪያዎች መካከል የማረሻ ትራክተር ፣ የሰብል ማጨጃ መሳሪያ ፣ መውቂያ እና ለመስኖ የሚያገለግል የውሀ መሳቢያ ከቀረጥ ነፃ ከሚገቡት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ከአምስት ዓመታት በፊት በተጠና ዓለም አቀፋዊ ጥናት ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት በእስያ ካሉ አገራት ጋር ሲነጻጸር የውሃ መሳቢያዎችን በመጠቀም የማልማት ሒደት ገና ለጋ ዕድሜ ላይ መሆኑን ይጠቁማል። ይሁን እንጂ የዕድገት ግስጋሴው ግን በከፍተኛ መጠን መጨመሩንም አያይዞ ይገልጻል።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013


