አዲሱ ሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ረቂቅ ፖሊስ ሰዎች በዘርፉ ተሰማሩ ወጣቶችም ሆኑ የትኛውም ማኅበረሰቡ ክፍል አካል የሆኑ ሰዎች የገንዘብ ለማግኘት ሀሳባቸውን ብቻ አስይዘው መበደር የሚያስችል እንደሆነ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጥራትና አዕምሮአዊ ንብረትን በተመለከተ የጥራት ቁጥጥር እንዲሁም የአዕምሮአዊ ንብረትን በተመለከተ ፖሊሲው ያላቸውን ሀሳብ አስይዘው ብድር የሚበደሩበት መንገድ እንዲኖር እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል።
አዲሱ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ረቂቅ ፖሊሲ የቴክኖሎጂ ባለቤት እንድንሆን ፣ ቴክኖሎጂውን እንድናለማ ፣ በቴክኖሎጂ የተደረጀ የመረጃ አያያዝ እንዲሁም ከሳይንስ የሚገኙ ግኝቶችን ወደ ውጤት የሚያደርስ ነው ሲልም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ረቂቅ ፖሊሲው ስራ ላይ ያለው ፖሊሲ ያላሳተፋቸውን ፈጠራን ማዕከል ማድርግ ፣ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የመሪነት ሚና እንዲወጣ የማያደርግ የቴክኖሎጂ ልማት ከኢኖቬሽን ጋር በሚፈለገው መልኩ ያላስተሳሰረ መሆንን ለመቅረፍ ታስቦ እንደተከለሰም ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፖሊሲ እስትራቴጂ እና ፕላኒንግ ዳይሬክተር ደስታ አበራ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በ2004 ዓመት የነበረው እስካሁን የምንጠቀምበት ፖሊሲ ክፍተቶች ስለነበሩበት እየተሻሻለ እንዳለ ጠቁመዋል።
በዋናነት እየተሰራበት ያለው ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ የማያደርግ የቴክኖሎጂ ልማት ከኢኖቬሽን ጋር በሚፈለገው መልኩ ያላስተሳሰረ ነበር ብለዋል።
የቀደመው ፖሊሲ በተለይም ቴክኖሎጂ ላይ ከውጪ አገራት የሚመጡትን የሚደግፍ ፣ ገልብጦ ከውጭ አገር ማምጣት ፣ የምርምር ስራውን የማይደግፍ እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ትኩረት የነፈገ እንደነበር ጠቅሰዋል።
የተሻሻለው ፖሊሲ ለቴክኖሎጂ ባታ በመስጠት ከውጭ አገራት የሚገቡትን ቴክኖሎጂዎች ማሳደግ ብቻ ሳይሆን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጓል፣ በስራ ፈጠራ ላይ ዘርፉ በከፍተኛ መጠን መስራት እንዳለበትም ጠቅሷል፣ ከሳይንስ ለሚገኙ ግኝቶች ፈጠራዎችን ያበረታታል ወደ ውጤትም እንዲቀሩ ያደርጋል እንዲሀም ለግሉ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ የቴክኖሎጂው መሪ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።
የኢኖቬሽን እና ኢንተር ፕራይዞች ተወዳዳሪነት ወጣቶች ማብቃት ላይ ፖሊሲው ትኩረት ማድረጉን የተናደሩት ዳይሬክተሩ እንደ ኢትዮጵያ ላለች 70 በመቶ ወጣት ላለባት አገር የተማረውን ወጣት ወደ ስራ ለማስገባት በቴክኖሎጂ ተደግፎ ዘርፎችን በማብዛት ትናንሽ ኢንተር ፕራይዞችን ማሳደግ እንደሚገባም በፖሊሲው መካተቱን ተናግረዋል፤በዚህም በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ኢንተርፕራይዝ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ትብብርና ትስስር በዋናነት ሁሉንም በፖሊሲው የተጠቀሱ ነገሮችን እንዲሳኩ ያግዛል በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ትስስር ሊኖር እንደሚገባ እንዲሁም አገራችን ላይ ያሉ ተቋማት ለአንድ አገር ስለሆነ የሚሰሩት ከፉክክር ይልቅ ተባብሮ መስራት እንዲያስችል በቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኖቬሽን መደገፍ እንዳለበት መጠቀሱን ገልፀዋል።
እንዲሁም በፖሊሲው አካባቢ ማህበራዊ እና ባህላዊ የልማት ልማቶቻችንን ያማከለ ሲሆን ከተለያዩ ነገሮች ጋር ቴክኖሎጂ የሚያመጣቸው ነገሮች የተለያዩ የአካባቢያችን ክፍሎች ወድቀው ይታያሉ ይህንን በቴክኖሎጂ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል እንዲሁም የህብረተሰቡን በቴከረኖሎጂ ማሰተሳሰር በዚህም ይህንን በቴክኖሎጂ ማደራጀት እንዳለበት በፖሊሲው መካተቱን አስታውቀዋል።
የፖሊሲ ክለሳው የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ጥናት፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ፣ የ10 አመት አገራዊ እና የዘርፍ ዕቅድ፣ ዘላቂ የልማት ግቦች 2030፣ የአፍሪካ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ 2024 እንዲሁም አለም አቀፋዊ ልምዶችን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ እንደሆነም አስታውቀዋል፤ፖሊሲው የሚፈለገው ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ በሚመለከተው አካል ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ሲሉ የዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013



