የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ ከቆሻሻን ከመለየት፣ ከማስወገድና መልሶ ከመጠቀም ጋር የተገናኙ ስድስት አዲስ ብሄራዊ ደረጃዎች ማውጣቱን አስታወቀ።
ከቤት ውስጥ ጀምሮ ሁሉም ዜጋ ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ቆሻሻን ከመለየት እና ከማወገድ አንጻር ከጸደቁት ስድስት ብሄራዊ ደረጃች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ከቆሻሻ ልየታ ጋር ተያይዞ የወጣው የተለየ አጽኖት እንደተጠው ተገልጿል።
ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ የወጣው ይህ ቆሻሻን የመለየት እና የማወገድ ደረጃ ከቤት የሚጀምር ሲሆን ከቆሻሻ ልየታ ጋር በተያያዘ አደገኛ ኬሚካል ያላቸውን ቆሻሻዎች እና ተመልሰው በቀላሉ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ቆሻሻዎችን እንዴት ነው የሚለየው እና የሚወገደው የሚለውን ለማሳወቅ የተቀመጠ ደረጃ መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።
ኤጀንሲው ይህንንም በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ በቀለም የሚገለጽ ደረጃ በአረንጓዴ፣ሰማያዊ፣ቀይ እና ጥቁር መለያዎች (ከለር ኮዲንግ) እንደተዘጋጀ አስታውቋል። ደረጃው ተግባራዊ ሲደረግ በርካታ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል። እሰከዛሬ ድረስ ቆሻሻን የምናስወግደው ለመለየት በማያስችል መልኩ ስለሆነ ይህ አይነት የቆሻሻ አወጋገድ መቅረት ስላለበት የደረጃዎች ምክር ቤት ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ተገልጿል።
የቆሻሻ መለየት እና የማወገድ ደረጃ የልየታ ሥርዓቱ ከቤት የሚጀምር ሲሆን በቤት ውስጥ ከማዕድ ቤት የሚወጡ የተለያዩ የድንች፣ የሽንኩርት፣ የካሮት እና የፍራፍሬ ልጣጮች እና የመሳሰሉት ተመልሰው ለማዳበሪያ ኮምፖስትነት ስለሚውሉ መልሶ ለመጠቀም ምቹ በመሆናቸው ለብቻ መወገድ ይችላሉ እነዚህ ከግብርና አገልግሎት ጋር ስለሚገናኙ በአረንጓዴ ከለር እንደሚወከሉ ተገልጿል።
ሌላው ደግሞ በቀላሉ ወደ ሌላ ምርት እንደገና መልሰን ልንጠቀምባቸው የምንችል ወረቀቶች፣የፕላስቲክ ምርቶች፣ጠርሙሶች እና ካርቶኖች እንዲሁም የብረታ ብረት ቁርጥራጮች በልዩ ሁኔታ መወገድ እና እንደገና ጥቅም ላይ መዋል ይችላሉ በሰማያዊ ከለር ተወክለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በቀይ ወይንም በሰማያዊ ቀለም የተወከሉ አደገኛ የኬሚካል ይዘት ያላቸው እንደ ባትሪ ድንጋይ ያሉ እና የኤሌክትሮኒክስ ውጤት የሆኑ ቶሎ የማይበሰብሱ እንዲሁም የሕክምና መሥጫ ስፍራዎች ውስጥ በመቃጠል የሚወገዱ የማይበሰብሱ ቆሻሻዎች በጥንቃቄ መወገድ እንዳለባቸው ተገልጿል።
ከዚህ በፊት ሁሉንም አይነት ቆሻሻ በአንድ ላይ አንድ ቦታ የመድፋት አወጋገድ መኖሩ ይታወቃል። ለቆሻሻ አወጋገድ አዲስ ደረጃ መውጣቱ ከተገለጸበት ማክሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2013 ጀምሮ ሁሉም በየቤቱ ልምምድ እንዲያደርግ ልጆችን ከማዋለ ሕጻናት ጀምሮ በማስተማር ገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር ላይ ያለንን ሀብት አንድንጠብቅ በሁሉም ተቋም ኀላፊነት ሊወሰድ ይገባል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን የ285 ብሔራዊ የጥራት ደረጃዎችን በብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ማፅደቁን ገልጿል። በስድስት ዘርፎች ተዘጋጅተው ከቀረቡት 285 ደረጃዎች 148 ያህሉ አዲስ ሲሆኑ፣ 44 የሚሆኑት የተከለሱና የተቀሩት 93 ደረጃዎች በፊት የነበሩና እንዲቀጥሉ የተወሰኑ እንደሆኑ አስታውቋል።
እነዚህም በግብርናና በምግብ ዝግጅት 18፣ በመሠረታዊና አጠቃላይ የደረጃ ዝግጅት 28፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች 72፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ 79፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል 69፣ እንዲሁም በአካባቢና ጤና ደኅንነት 19 ደረጃዎች እንደሆኑ ታውቋል።
ወቅታዊውን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ የጤና መስጫ ተቋማትን የተመለከቱ 13 ደረጃዎች ወጥተዋል። በኮቪድ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ከመኖሩ ጋር በተያያዘ የፋይናንስ እንቅስቃሴው ወደ ዲጂታል እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው 28 የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከቱ ብሔራዊ ደረጃዎች መውጣታቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንዳለው መኮንን ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013



