በደብረ ብርሃን የኃይሌን ጨምሮ 7 ሆቴሎች መሬት ተረክበዋል
በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በሆቴል ኢንቨስትመንት የተሰማራው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በሰሜን ሽዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በ550 ሚሊዮን ብር ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ሊገነባ ነው።
አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረ ስላሴ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል የግንባታ ሥራ መጀመሩ ተመላክቷል። የሀይሌ ሪዞርት ዋና ማናጀር መልካሙ መኮንን ለአዲስ ማለዳ አንዳሉት ከሆነ የሆቴል ግንባታው ከኹለት ዓመት በታች በፈጀ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የሆቴሉን ግንባታ የሚከናውነው ድርጅት ጀረታ ኮነሱለታንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መሆኑን መልካሙ ተናግረዋል። አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረ ስላሴ በደብረ ብርሃን ከሚገነባው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል በተጨማሪ አራት ሆቴሎችን እየገነባ መሆኑን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል በ8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፋል ነው የተባለው። ሆቴሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከ300 ላይ ዜጎች በቀጥታ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚታሰብ መልካሙ ጠቁመዋል። በአሁኑ ስዓት በአትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ ተገንብተው ሥራ ላይ የሚገኙ በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ሆቴሎች ለ1500 በላይ ዜጎች ሥራ እድል ፈጥረዋል።
ሀይሌ በሥራ ላይ ካሉት ሆቴሎች ውስጥ በጎንደር ከተማ ከሚገኘው በሊዝ ኪራይ ስምምነት ከሚሠራው ከጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል በስተቀር ሁሉም ሆቴሎች በራሱ የተገቡ መሆናቸውን መልካሙ አስታውሰዋል።
የደብረ ብረሃን ከተማ ኢንቨስትምት ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ አለማየሁ ጥላየ ሀይሌ በደብረ ብርሀን የሚገነባው ሆቴል መሬቱን እንዳገኘ በፍጠነት ወደ ግንባታ መግባቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አለማየሁ አክለውም ሀይሌ ሆቴል ግንባታውን ከማፋጠና ባለፈ የከተማዋን ኢንቨስትመንት በትብብር እያገዘ ነው ብለዋል።
አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሀይሌ በተጨማሪ በከተማዋ በሆቴል ኢንቨስትምንት ለመሳተፍ ቀደም ብለው ጥያቄ ያቀረቡ ስደስት ድርጅቶች የሆቴል ግንባታ መሬት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። በተጨማሪም 13 ድርጅቶች በደብረ ብርሃን ሆቴል ለመገንባት ለአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ጥያቄ አቅርበው ፈቃድ እየተጠባበቁ ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ባለ ኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በላይ ደበበ፣ አጋዝ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፣ መገዘዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፣ አማዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፣ ሽዋ ብርሀን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድረጅትና ሀብታሙ ሎጅ አንደሆነ አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ደብረ ብርሃን በአከባቢው ባለው ሰላምና የኢንቨስትምንት ምቹነት አማካኝነት በርካታ ኢቨስትመንት ፍሰቶችን እያስተናገድች ሲሆን፣ ወደ ደብረ ብርሃን ከሚፈሱት የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሆቴሉ ዘርፍ አንዱ ነው።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ወደ ከተማዋ የሚፈሱ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን በይሁንታ በመቀበል የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች እየመለሰ መሆኑን አስታውቋል። ወደ ደብረ ብርሃን ለኢንቨስትመንት የሚመጡ ባለሀብቶችን እንደሚፈደግፍና እንደሚበረታታም ነው ከተማ አስተዳደሩ የገለጸው።
በደብረ ብርሃን የሚታየው የኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ የሰፋ እንደሆ አለማየሁ ጠቁመዋል። ይሁን አንጅ ደብረ ብርሃን ከተማ የሚቀርቡላትን የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በደረጃ እየፈቀደች ነው ብለዋል።
ኃይሌ ገብረሥላሴ በቅር የገበታ ለአገር እንቅስቃሴ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሚገኘው የጎርጎራ ከተማ ላይ ሰፊ የሆቴል ኢንቨስትመንት ለመጀመር ፍላጎት እንዳሳየ መናገሩ ሚታወስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013



