የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የደሞዝ አከፋፈል ቅሬታ እንዳላቸው ገልጹ

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሠራተኞች በተመሳሳይ የሥራ እና የትምህርት ደረጃ ሰፊ ልዩነት ያለው የደሞዝ አከፋፈል ላለፉት ኹለት ዓመታት እንደሚከፈላቸው እና ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ለኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ቢገልጹም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ተቋሙ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ተብሎ ከተሰየመበት እና ተመሳሳይ ተግባር የምናከናውን ሠራተኞች አንድ ላይ መሥራት ከጀመርንበት ሐምሌ 2011 ጀምሮ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ እየሠራን እና ተመሳሳይ የሥራ ልምድ እንዲሁም የትምህርት ደረጃ እያለን የተጋነነ የደሞዝ ልዩነት አለ ብለዋል።

ሠራተኞቹ በሲቪል ሰርቪስ የአከፋፈል ሥርዓት ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ያልተከፈለን ውዝፍ ክፍያ ወይንም (JEG) በተመሳሳይ ኹለት ዓመት እንዳልተከፈላቸው ገልጸዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ቢሮዎች ጭምር የሚሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ቅሬታው መኖሩን አምነው በኃላፊነት ደረጃ የምንሠራ ሰዎች ሁሉ የደሞዝ ክፍያ ቅሬታ አለብን ጥናት ተጠንቶ እንዳለቀ ቢነገረንም ተግባራዊ አልሆነም ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃይል ልማት የቢሮ ኃላፊ ኃይሉ ሉሌ በአጠቃላይ በዚህ አገር ላይ የነበረው የደረጃ ምደባ እና የደሞዝ አከፋፈል ሥርዓት የተለያየ እና ከ40 የሚበልጥ እንደነበር ገልጸው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት Job Evaluation and Grading (JEG) ተሠርቶና ጥናት ተደርጎ በሥራ ምዘና ደረጃ በመስጠት ተግባራዊ ካደረጉ ቦታዎች መካከል አዲስ አባበ አንዷ ብትሆንም የኛ መሥሪያ ቤት ግን ተግባራዊ አላደረገም ነበር በማለት ገልጸዋል።

ይህ አሠራር ተግባራዊ ከተደረገባቸው ቦታዎች በኹለት መልኩ እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች መኖራቸውን እና አንደኛው ደረጃ ዝቅ አለብን የሚል ሲሆን ኹለተኛው ሥም እና ስያሜ ላይ የሚነሳ ቅሬታ እንደሆነ ተገልጿል።
ደረጃ ዝቅ አለብን ለሚለው መዛኙ አካል ወይንም ተመዛኙ ሠራተኛ በአግባቡ አልሠሩም ማለት እንጂ ሲስተሙ ያስገቡለትን መረጃ የሚያወጣ በመሆኑ ቅሬታ እንደማያስነሳ እና በፌዴራል መንግሥት ሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤት የሚሠራ በመሆኑ አሠራሩ ተመሳሳይ እና በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ እና የሥራ ልምድ ተመሳሳይ ክፍያ የሚከፍል ነው ብለዋል።

ከዚህ ሁሉ አልፈው ትክክል ናቸው ተብለው የታመኑ ቅሬታዎች ደግሞ ወደ ፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይላካሉ በማለት ገልጸዋል። ኃይሉ በተለየ የእኛን መሥሪያ ቤት ቅሬታ ስመለከት ቅሬታው የመጣው በኹለት መንገድ ነው። አንደኛው ተቋሙ የሦስት ተቋማት ውህድ በመሆኑ እና ሠራተኛው ሦስት አይነት የደሞዝ አከፋል ሲከፈለው የነበረ በመሆኑ ማለትም በልዩ እስኬል የሚከፈል፣ በፕ/ሳ መደብ የሚከፈሉ እና መካከለኛ ደሞዝ ያላቸው በመሆናቸው መሥሪያ ቤቱ በJEG ደሞዝ አከፋፈል ሥርዓት ለመክፈል ሲሞክር ደረጃውን ያለፉ ተከፋዮች መኖራቸው አንዱ ችግር ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል።

የቢሮ ኃላፊው በJEG የደሞዝ አከፋፈል መሠረት ደሞዝ ሲሠራ ከፍ እና ዝቅ ሊል ስለሚችል በፊት በዳይሬክትር ደረጃ የነበረ ሰው አሁን በባለሙያ ደረጃ ሊሆን ይችላል። ደሞዙ ግን እንደተጠበቀ ሊቆይ ይችላል። በባለሙያ ደረጃ የነበረ ደግሞ ዳይሬክትር የመሆን እድል ቢኖረውም ደሞዙ ሳይጨምር ሊቀጥል ይችላል። በዚህ ጊዜ ተመሳሳይ ሥራ ላይ የተለያየ ክፍያ እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ሰዎች ሥራ ሲለቁ፣ በሕይወት ሳይኖሩ ሲቀሩ እና ጡረታ ሲወጡ አዲስ የሚቀጠሩ ሰዎችም በJEG መሰረት በመሆኑ ተመሳሳይ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም ብለዋል። ነገር ግን JEG ተግባራዊ ሲደረግ ወደ እኛ ተቋም ባለመድረሱ አሁን ተመዝኖ አልቆ ተግባራዊ ተደርጓል። ደብዳቤ ተጽፎ ከሐምሌ 2012 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ያለው ያልተከፈለ የደሞዝ ጭማሪ ክፍያ በዚህ እንዲከፈል በደብዳቤው ተገልጿል በማለት አሳውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here