በአዲስ አበባ የሚገኙ አራት የሙስሊም ማኅበራት የዑለማኦች የጋራ መግባቢያ ሰነድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውይይት ቀርቦ እንዲጸድቅ፣ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ያለበትን ወቅታዊ አቋም አስመልክቶ ሐሙስ መጋቢት 16/2013 በሃይከን ሆቴል በሰጡት የጋራ መግለጫ ጠየቁ ።
የጋራ መግለጫውን ያወጡት አራቱ የሙስሊም ማኅበራት ዳናአህሉ ሱና ወልጀማዓ ዑለማ ማኅበር፣የአዲስ አበባ ኢማሞች ማኅበር፣የኦሮሚያ አህለ-ሱና ዑለማ ማኅበር፣የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣት ማኅበር ናቸው።
በሚያዝያ ወር 2011 በሸራተን ሆቴል ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ፣ ላይ በይደር እንዲቆይ ተደርጎ እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ቀን ለውይይት እንዳልቀረበ የተገጸው የዑለማ የጋራ መግባቢያ ሰነድ፣የመጅሊሱ መተዳደሪያ ደንብ እና ሌሎችም ተነስተው በነበሩ ቅሬታዎች እና ጉዳዮች ላይ ባለ 10 ነጥቦች መግለጫ አውጥል።
በመግለጫው ላይ በተደጋጋሚ የተነሱት ቅሬታዎች በሚያዝያ ወር 2011 በሸራተን ሆቴል ከተደረገው ስብሰባ ጋር የተገናኙ ሲሆኑ የመጀመርያው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአገራዊ ለውጡ አንድ አካል እንዲሆን ታስቦ መጅሊሱ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የሚያስችለውን ጥናት የሚያቀርብ ዘጠኝ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል።
ይህ ዘጠኝ ኮሚቴ ከሠራቸው የጥናት ሰነዶች ውስጥ የዑለማዎች የጋራ መግባቢያ ሰነድ እና የመጅሊሱ መተዳደሪያ ደንብ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በእነዚህ ሰነዶች ላይ ለመወያየት ሚያዝያ 23/2011 በሸራተን ሆቴል ስብሰባ ተጠርቶ ዑለማኦች ከየክፍለ አገሩ ተጉዘው ስብሰባው ላይ ለመገኘት አዳራሹ በር ላይ የተገኙ ቢሆንም በዕለቱ የሱፍያውን መስመር በመወከል ለስብሰባው የተላኩ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ወደ አዳራሹ አትገቡም በሚል ግርግር በመፍጠር ዑለማኦች ለሰዓታት ከአዳራሹ ውጪ እንዲንገላቱ ተደርጎ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል።
ወደ አዳራሹ ከተገባም በኋላ ለውይይት ይቀርባል የተባለው የዑለማኦች የጋራ መግባቢያ ሰነድ መድረክ ላይ አዘጋጆቹ ካነበቡት ውጭ ሰነዱ ለውይይት ሳይቀርብ እና በዑለማዎች የጋራ መግባባት ሳይፀድቅ ስብሰባው እንዲበተን መደረጉ የዑለማኦቹን ክብር ያልጠበቀ እና ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድ የሚሆንበትን ትልቅ እድል አጭበርብሮ ለማለፍ የተሞከረበት ስለሆነ በሚያዝያ 23/2011 በሸራተን ሆቴል ላሊበላ አደራሽ ዑለማኦች ላይ የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት በፅኑ እናወግዛለን በማለት ይገልጻል።
በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ሸራተን ላይ በተደረገው ስብስባ በይደር እንዲቆይ ተደርጎ እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ቀን ለውይይት ያልቀረበው የዑለማእ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዑለማኦች ለውይይት ቀርቦ የኢትዮጵያ ሙስሊም አንድነቱን ለማጠናከር ትልቅ መሰረት ይሆናል ተብሎ የታመነበት የዑለማእ የጋራ መግባቢያ ሰነድ እንዲፀድቅ እና ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን ጠብቆ ጊዜ፣ ሃብትና ጉልበቱን ለአገር ሰላምና ልማት ማዋል የሚችልበት እድል በአፋጣኝ እንዲመቻች መግለጫው አትቷል።
በሌላ በኩል በዘጠኙ ኮሚቴዎች ተሰናድቶ የቀረበው እና የመጅሊሱን ነባር መዋቅር ለመተካት ታቅዶ የተዘጋጀው የመጅሊሱ መተዳደሪያ ደንብ ልክ እንደ የዑለማኦች የጋራ መግባቢያ ሰነድ ሁሉ ለውይይት ያልቀረበ በመሆኑ በዘርፉ ብቁና ልምድ ያላቸው ሙስሊም ምሁራን ጥልቅ ውይይት እንዲያደርጉበት፣ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ አንድነትና ሰላም አስጠብቆ መሳጂዶች ከሚያዝያ 23/2011 በፊት በነበሩበት ይዞታ ሥር ሆነው እንዲቀጥሉ በሚያደርግ አግባብ አቅም በፈቀደው ልክ በፍጥነት ለዑለማ ምክር ቤቱ ቀርቦ በዑለማኦቹ መሪነት እንዲፀድቅ እና ተግባር ላይ እንዲውል አበክረን እንጠይቃለን በማለት ገልጸዋል።
በወቅቱ በነበረው ቦርድ በተፈፀመው የአሠራር ክፍተት ለሀጅ ወደ ሳዑዲ ሳይሄዱ የቀሩ እና እስካሁን ድረስ ገንዘባቸው ላልተከፈላቸው መጅሊሱ ገንዘባቸውን ተመላሽ እንዲያደርግላቸውወይም ተመጣጣኙን ካሳ በአስቸኳይ እንዲከፍላቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



