ደረጃው የታክሲ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሱ የደኅንነት ችግሮችን ለማስቀረት የሚረዳ ነው
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በቴክኖሎጂ ታግዘው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችና አሽከርካሪዎች ሊመራ የሚችል ረቂቅ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኘው ረቂቅ ደረጃ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችንና አሸከርካሪዎችን የሚሰጡትን አገልግሎት የሚወስን የታክሲ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ደረጃ ሲሆን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ አዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ እንደተሳተፉበት እሱእንዳለ ሸዋንዳኝ አስታውቀዋል።
በመጀመሪያ ረቂቅ ደረጃ ላይ የሚገኘው የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ በቴክኖሎጂ ታግዘው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ራይድ፣ ፈረስ፣ ዛይ ራይድና መሰል አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ተቋማትንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ዝቅተኛ ማሟላት የሚገባቸውን መስፈር ለመወሰን የተዘጋጀ ደረጃ እንደሆነ ተናግረዋል።
ደረጃው በመላው አገሪቱ መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን የማከለ መሆኑ እና በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ረቂቅ ደረጃ ኹለት መሰረታዊ ነገሮች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ እሱእንዳለ ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡት ድርጅቶች(ኦፕሬተሮች) ወይም መሰል አገልግሎት በግለሰብ ደረጃ የሚሰጡ አካላት ላይ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ግዴታን የሚጥል ነው ተብሏል።
ኹለተኛው በድርጅቶች ሥር የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ይሁን በግለሰብ አሸከርካሪዎች ላይ ማሟላት ያለባቸውን ዝቅተኛ መስፈርት እንዲያሟሉ ኃላፊነት የሚጥል እንደሆነ ተነግሯል።
የታክሲ ትራንስፖርት የሚሰጡ ድርጅቶች (ኦፕሬተሮች) ባሰማሯቸው አግልግሎት ሰጭ ታክሲዎች ላይ መሰረታዊ የሆኑ የደህንነት መሳሪያዎችን እንዲስገጥሙ ኃላፊነት የሚጠል ሲሆን፣ የካሜራ፣ የመረጃ ሪከርደርና ጅፒኤስ እንዲኖራቸው የሚያዝ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል።
በሹፌሮች (አሽከርካሪዎች) ላይ የሚጥለው ግዴታ ደግሞ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የተሻለ አግልግሎት እንዲሰጡ፣ የአሽከርካሪ መታወቂያ በግልጽ እንዲለጥፉ፣ የተሽከርካሪው ጽዳትና የጤና ጉዳዮችን ያካተተ ግዴታ የሚጠል እንደሆነ ነው ኃላፊው የጠቆሙት።
ደረጃው የታክሲ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሱ የደህንነት ችግሮችን ለማስቀረት ያለመ መሆኑን እና የታክሲ ኦፕሬተሮችና አሽከርካሪዎች በደንበኞቻቸው ላይ የሚደርሱ የደህንነትና የንብረት መጥፋት ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነ ታውቋል።
በተጨማሪም የታክሲ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች(ኦፕሬተሮች) የመረጃ ሪከርድ የመያዝ ኃላፊነት በተጣለባቸው መሰረት ያከማቹት መረጃ በየዓመቱ ለተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቀርቦ እንደሚገመገም ረቂቅ ደረጃው አስቀምጧል።
የደረጃው አስፈላጊነት ሀሳብ የመነጨው በኢትዮጵያ የታክሲ አገልገሎት ሰጭዎች(ኦፕሬተሮች) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸውና በዘፈቀደ መሥራታቸው ፣በአገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የደህንነት ችግር እያጋጠመ በመሆኑ ወጥ የሆነ የሚመሩበት ደረጃ በማስፈለጉ መሆኑን እሱእንዳለ ገልጸዋል።
ደረጃውን ለማዘጋጀት የካናዳ እና የአውስትራሊያ ልምድ መጠቀማቸውን ነው እሱእንዳለ የጠቆሙት።
የታክሲ አገልግሎት የራሱ የሆነ ሙያ ስነምግባር የሚጠይቅ፣ተሳፋሪዎችን ምቾት የሚያሟላና ደህንነታቸውን የሚጠብቅ ነው ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመጠቀም በአገልግሎት ሰጪዎች ጥረት ቢደረግም፣ በሌላ በኩል በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግሮችም እንዳሉ ነው የተገለጸው።
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የተሳፋሪዎች መብትና ግዴታ፣ የታሪፍ፣ የስርቆት፣ ማጭበርበር፣ የአሽከርካሪዎች ስነምግባርና የመሳሰሉት ችግሮች ሲስተዋሉ ይታያሉ። ለዚህም ዋነኛው ችግር ወጥ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ አለመኖሩ እንደ አንድ ችግር ነው ተብሏል። ምንም እንኳ ዘርፉን የሚቆጣጠረው የመንግስት አካል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲኖር መመሪያዎችን በየጊዜው ቢወጡም ቀጣይነት ያለው መሻሻሎችን አምጥተዋል ማለት ግን አይቻልም ተብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



