በመተከል ዞን ቡለን ከተማ ነዋሪዎች ስጋት ገብቶናል በማለት ቤተሰባቸውን እያሸሹ ነው

0
824

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ግጭትና ሞት ያልተለየው መተከል ዞን ቡለን ከተማ የሚኖሩ ዜጎች የታጠቀ ኃይል ከተማ ገብተው መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ባደረባቸው ስጋት ቤተሰቦቻቸውን እያሸሹ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የቡለን ከተማ ነዋሪዎችን ሽሽት ያስከተለው ጉዳይ ዞኑን የሚስተዳድረው ኮማንድ ፖስት በዞኑ በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ከሚፈጽመው ታጣቀ ኃይል ጋር ድርድር አደርጋለሁ የሚል አካሄድ መጀመሩን ተከትሎ የታጠቁ ኃይሎች በድርድርና በትጥቅ መፍታት ሰበብ ከተማውን እያጠኑ መሆኑን ተከትሎ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በስጋት ከተማዋን ለቀው የወጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በታጠቀ ሀይሉ እንቅስቃሴ ሙሉ ቤተሰባቸውን ይዘው ከሸሹት ውስጥ መሰለ መስፍን(ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) እንዳሉት ባለቤታቸውንና ኹለት ልጆቻቸውን ይዘው ከቡለን ከተማ ባደረባቸው ስጋት አባታቸው ወደ ሚገኙበት ወደ ኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ መሄዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መሰለ ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ አባታቸው ያቀኑት ምንም አይነት ንብረት ሳይዙ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። “በገጠሩ አካባቢ የነበረው ስጋት ለወትሮው ከተማ ላይ አያሰጋም ነበር፣ ከሳምንት በፊት ግን የታጠቀ ኃይል በቡለን ከተማ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውና አንዳንድ የዘረፋ እና ጥቃቶች ዝንባሌ መታየታቸው ስጋት ስለፈጠረብኝ ልጆቼን አላስገድልም ብየ ባዶ እጄን ወደ አባቴ ጋር እየሄድኩ ነው።” ብለዋል መሰለ።
መሰለ በቡለን ከተማ በመንግሥት ሥራ ላይ የሚተዳደሩ ቢሆንም ቤተሰባቸውን ከስጋት ነፃ ሆነው በከተማዋ መቀጠል እንዳልቻሉ ነው የሚገልጹት።

አዲስ ማለዳ አካባቢው ከሚገኙ ምንጮቿ እንዳረጋገጠችው ከሆነ በቡለን ከተማ የጸጥታ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ንብረታቸውን ትተው ወደ ሌላ አከባቢ በማቅናታቸው የታጠቀ ኃይል ንብረት እየዘረፉ ነው ተብሏል።
በክልሉ ከሚፎካከሩት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መጋቢት 12/2013 ባወጣው መግለጫ ይህንኑ የዜጎች ስጋት የሚረጋግጥ ሀሳብ አንጸባርቋል። ፓርቲው በመግለጫው “በመተከል ዞን የተከሰተው የዜጎች እልቂትና ሞት እንዲሁም መፈናቀልን ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥት የሚመራ ኮማንድ ፖስት ከመስከረም 11/2013 ጀምሮ መዋቀሩ የሚታወቅ ሲሆን በመሃል አንፃራዊ የሰላም ጭላንጭል ቢታይም ሰሞኑን ግን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት አለመረጋጋት እየተመለሰ ይገኛል።” በማለት ተናግረዋል።

“በተለይ በቡለን፣ በድባጤ እና ወንበራ ወረዳዎች አሁንም ተደጋጋሚ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ቀጥሏል።
ዞኑን እያስተዳደረ የሚገኘው ኮማንድ ፖስትና የክልሉ መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት መከላከል አልቻሉም። አርሶ አደሩ ሰብሉን መሰብሰብ አልቻለም። ለመጭው የክረምት የግብርና ሥራም ዝግጅት ማድረግ አልተቻለም። ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርት መመለስ አልቻሉም” ሲል ፓርቲው በላከልን መግለጫ ገልጿል።

አዲስ ማለዳ በ123 ዕትሟ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከተማ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን አነጋግራ የአካባቢውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የመንግሥት እርምጃ ወደ ስጋት ተቀይሮብናል ማለታቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።
ነዋሪዎቹ ይህን ያሉት በመተከል ዞን በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ጥቃት የሚደርሰው ታጣቂ ሀይል ቡለን ከተማ ለድርድር በሚል ሰበብ እየወጣ አና እየገባ ለነዋሪዎች ስጋት መሆኑን በመግለጽ ነበር።
በሌላ በኩል በዞኑ ባሳለፍነው ሳምንት በዚሁ ቡለን ወረዳ ዶቢ ቀበሌ የታጠቁ ኃይሎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመስጋት ነዋሪዎቹ መሸሻቸውን አዲስ ማለዳ ከአካባቢዎቹ ኗሪዎች ሰምታለች።
አዲስ ማለዳ የነዋሪዎቹን ስጋት ይዛ የቡለን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግዛቱ ነሲ ጋር በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ብትደውልም፣ ስላካቸውን ሊመልሱ አልቻሉም።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here