ሜድሮክ ጎልድ ፈቃድ ሊታደስለት ነው

0
975

በኹለት ዓመታት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል

የኢትዮጵያ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ሜድሮክ ጎልድ ለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ድርጅት ከሦስት ዓመት እገዳ ብኋላ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፈቃድ ለማደስ መስማማቱ ተገለፀ።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እንደገለፀው ፋብሪካው ታገደ የፈቃድ እድሳት ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ በፕሮጀክቱ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍል ካሳ ካስጠበቀ ብቻ ነው ፍቃዱ የሚታደስለት ተብሏል።
ድርጅቱ በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት ውስጥ አቋርጦት የነበረውን ወርቅ የማውጣት ሥራ እንደገና ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሜድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከ2010 ግንቦት ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር መታገዱ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጅ ሜድሮክ ፈቃዱ የሚታደስለት ቀደም ሲል በፕሮጀክቱ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን ካሳ ከከፈለ በኋላ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በዘላቂ ጥቅም ላይ ስምምነት ላይ ሲደርስ መሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል።
ሜድሮክ ጎልድ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ያለ ሥራ መቆየቱ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት ሊቸገር እንደሚችል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፍሬህይወት ፍቃዱ ከኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ፍሬህይወት አክለውም ሥራ አቁሞ የቆዩ ማሽነሪዎች መጠገን ስላለባቸው ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ወደ ሥራ መግባት የማይችል ሲሆን ነገር ግን ማሽነሪዎቹ ተጠግነው ካለቁ በኋላ የወርቅ ማውጣት ሥራው እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የሜድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ ከግንቦት 1/2010 ጀምሮ የታገደው፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ሜድሮክ ጎልድ በለገደምቢ በሚያካሂደው የወርቅ ማዕድን ልማት ሥራ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የድርጅቱ የምርት ሂደት የአካባቢ ብክለት እያስከተለ ነው የሚል ቅሬታ ማንሳቱን ተከትሎ ነበር።

በስፍራው ከ20 ዓመታት በላይ ማዕድን ሲያወጣ የቆየው ሜድሮክ ጎልድ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ፈቃዱ ለቀጣይ 10 ዓመታት መታደሱን ተከትሎ በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫን ወደ ሥራ የሚመልስ እቅድ በጥናት እንዲሁም በድርድር ተደግፎ መዘጋጀቱን ሜድሮክ ጎልድ በ2012 ይፋማድረጉ የሚታወስ ነው። ሜድሮክ ጎልድ ይህን ያስታወቀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ለአልሚዎች እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በማስወገድ አዲስ ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ ለመተግበር የካቲት 6/2012 ኢሊሌ ሆቴል ባለሀብቶችን ባወያየበት ወቅት ነበር።

የሥራ እቅዱ እንዲተገበር የጠየቀው ሜድሮክ ጎልድ ያቀረበው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኹለት ጥናቶች ተካሂደው ነበር። የእነዚህ ጥናቶችን አስተያየቶች እና ውጤቶች መሰረት በማድረግ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና በድርጅቱ የትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱን እና የመንግሥትን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተግልጾ ነበር።

ሜድሮክ ጎልድ በዓመት አራት ሺሕ ኪሎ ግራም ወርቅ ለውጭ ገብያ ያቀርብ ነበር። የኢትዮጵያ ወርቅ ወደ ውጭ መላክ አቅም ሜድሮክ ጎልድ ሥራ ማቆሙን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሜድሮክ ጎልድ ተዘግቶ በመቆየቱ 12 ሺሕ ኪሎ ግራም ወርቅ ለውጭ ገብያ የማቅረብ አቅሟን አጥታ ቆይታለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here