የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በሰጣቸው ፍቃድ መሰረት አገሪቷ ውስጥ ያሉ ቡናዎችን መቅመስ የሚቻልበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ ዋይልድ ኮፊ የተሰኘ አዲስ ድርጅት ተቋቀመ።
ቡና ለአገራችን ኢኮኖሚ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሲሆን፣ መንግስትም ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮùያ የቡና ጣዕሞች መቅመሻ ኮፊ ሀውስ፣ የኢፌድሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሂሩት ካሰው (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣናት በተገኙበት ሚያዚያ 16/ 2013 በይፋ ስራ ጀምሯል።
ዋይልድ ኮፊ በፍሬሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ስር የተቋቋመ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ ከቡና መቅመሻ ድርጅት ባለፈ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ቡና በቀጥታ በዶላር እንዲሸምቱ የሚያስችል አሰራርም መዘርጋቱን የዋይልድ ኮፊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገዛኸኝ ማሞ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ለዲፕሎማቶች እና ለቱሪስቶች የአገርን ትልቅ ገጽታ ለማስተዋወቅ ወጥኖ የተነሳው ድርጅቱ፣ ወደ ውጪ የሚላኩ ቡናዎች በዶላር የሚሸጡበት የመጀመሪያው ተቋም ነው ብለዋል።
ዋይልድ ኮፊ ሚያዚያ 11 /2013 ከብሔራዊ ባንክ ባገኘው ፍቃድ መሰረት የተቆላ የሀገር ውስጥ ቡናን በዶላር እንዲገበይ በማድረግ የአገሪቷን የዶላር እጥረት ለመቅረፍ የታሰበ መሆኑን ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ዋይልድ ኮፊ የመቅመሻ ቦታ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ7 በላይ የቡና አይነቶች ለመቅመስ የተቋቋመ ሲሆን፣ በተጨማሪም የቱሪስት መስህብ ለማስፋት፣ የአገር መልካም ገፅታ ለመገንባት እና ኢትዮጵያ የቡና መልከዓ-ምድር መሆኗን ለማንፀባረቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገዛኸኝ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ በአለም ላይ ሶስተኛዋ የአምባሳደሮች እና የዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ ትክክለኛውን ወደ ውጪ የሚላኩ ቡናዎችን ለመቅመስ የሚችሉበት ቤት ነው ተብሏል።
አዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት የሚቻለው ቡና ወደውጪ ከሚላኩት ቡናዎች የተረፈ ምርት በመሆኑ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ግኝት ቡናዎችን የሚቀመስበት ተቋም እስከ አሁን አልተቋቋመም።
ይህ የመቅመሻ ቦታ የተቋቋመው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ የቡና አቅርቦት ለማስተዋወቅ፣ ጣዕሞቹ እንዲለዩ እንዲሁም የዶላር እጥረትን ለመቀነስ ታስቦ ነው።
ከ15 ቀናት በፊት መስቀል ፍላወር አካባቢ ዋና መቅመሻ ቤቱን ከፍቶ ወደ ስራ የገባው ዋይልድ ኮፊ በቀጣይም ወደ ሳርቤት፣ ፒያሳ፣ቦሌ መድሐኒአለም እና ሲኤምሲ አድማሱን ለማስፋት ማቀዱን ሰምተናል።
ዋይልድ ኮፊ የመቅመሻ ቦታ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ለመስራት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ባለው የሴት ባሬስታ እጥረት ምክንያት ድርጅቱ ከሁለቱም ጾታዎች ለ22 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገዛኸኝ ነግረውናል።
ኢትዮጵያ 99 በመቶ ለአለም አገራት አረንጓዴ ቡናዎችን የምትልክ ሲሆን፣ ዋይልድ ኮፊ የተቆላ ቡናን ለአለም ለማስተዋወቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ፣ መልዕክት የሚያስተላፉ ፣ሙሉ በሙሉ ከቡና የተሰሩ አለምን ሲያጠጡ የሚያሳዩ ምስሎች በመስራት ቤቱን በዲፕሎማቶች በኩል ጥሩ እይታ እንዲኖረው ለማድረግ ተችሏል ሲሉ ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ፍሬሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ከሶስት ዓመት በፊት የተቋቋመ የተቆላ የቡና ላኪ ድርጅት ሲሆን፣ ምርቱን በሳውዲ አረቢያ ከ70 በላይ በሆኑ ሱፐርማርኬቶች ያከፋፍላል።
በተጨማሪም ወደ እንግሊዝ፣ጀርመን፣ማሊ እና ደቡብ አፍሪካ ቡናዎችን በመላክ እና በአገር ውስጥ ደግሞ ለሆቴሎች እና 95 በመቶ ለሚሆኑ ሱፐርማርኬቶች በማከፋፈል የሚታወቅ ድርጅት ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



