የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ ማዘጋጀቱን ገለጸ።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከተለያዩ አገርአቀፍ የሙያ ማኅበራት ጋር በመሆን ምክር ቤት ለማቋቋም ረቂቅ ማዘጋጀቱን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ታረቀኝ ገረሱ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሙያ ማህበራት የተደራጀ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተገልጿል። ከ220 በላይ የሆኑ የሙያ ማህበራትን በማስተባበርና ረቂቅ በማዘጋጀት ሂደት ላይ የከፍተኛ ትምህርት አግባብትና ጥራት ኤጀንሲ ሀላፊነቱን ወስዶ በመስራት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታዉቀዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምክር ቤት እንዲቋቋም ሃሳቡ የመነጨዉ ፣ የካቲት 16/2013 ኤጀንሲዉ ባዘጋጀዉ የሙያ ማህበራት የውይይት መድረክ ላይ ፣ የሙያ ማህበራቱ በሙያቸዉ በተደራጀ መልኩ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችል፣ “የተመቻቸልን ነገር የለም” ሲሉ ባነሱት ጥያቄ እና ቅሬታ መሰረት መሆኑ ተገልጻል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) የተለያዩ ጥናቶችን፣ የሌሎች አገሮችን የልምድ ተሞክሮ እና የሙያ ማህበራቱ ተነሳሽነትን በመዉሰድ ይህ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን በመቀበላቸው፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ምክር ቤት እንዲቋቋም ጥናቶችንና ልምዶችን ከሌሎች አገሮች በመዉሰድ የሙያ ማህበራትን በማስትባበር ረቂቅ ማዘጋጀቱን የኤጀንሲዉ የዳይሬክተሮች ዳይሬክተር ታረቀኝ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
የሚመሰረተው ምክር ቤት ዋናው አላማው፣ በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄደ ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ዓለም-አቀፍ ተሞክሮዎችን ጭምር በመዳሰስ በሁሉም የሙያ ዘርፎች ብቃት ያለው የሰው ሀይል በጥራት ለማፍራት የሚያስችሉ ደረጃዎችን እና አሰራሮችን በማቅረብ፣
በስርዓተ-ትምህርት ማሻሻያ ስራዎች እና በመሳሰሉት ላይ በመሳተፍ፣ የአገሪቱን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት እንዲሻሻል እና በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ሀይል ለማፍራት አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠር ነው።
ከአገር ዓቀፍ አልፎ ዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር የሚሰራ ምክር ቤት ተደርጎ ስለሚመሰረት በአገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ላይ በዘርፉ ከፍተኛ አተዋጽኦ ሊፈጥር የሚችል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲዉ ባገኘችዉ መረጃ ማወቅ ተችሏል።
ይህ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት በሙያ ማህበራት የሚመራና ከማንኛዉም ተጽእኖ ነጻ ሆኖ የሚንቀሳቀስና ቀጣይነት ያለዉ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ያሉ የሙያ ማህበራት በተደራጀ መልኩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያሥችል ነገር እንዳልነበረ እና አሁን የሚመሰረተዉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንን ኤጀንሲዉ አስታዉቋል። በሌሎች አገራት ላይ የሙያ ማህበርት በከፍተኛ ትምህርት ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም እንደተሞክሮ በማቋቋሚያ ረቂቁ ላይ እንደተወሰደ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የሚቋቋመው ምክር ቤት በገንዘብና ቁሳቁስ የራሱን የገቢ ምንጭ የሚያፈላለግ እና መንግሥትም ድጎማ እንዲያደርግ ጥያቄ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች ደረጃ ቤተ-ሙከራዎች፣ የእውቅና አሰጣጥ መመዘኛዎችና አገልግሎቶች ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚሳተፍ እና ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራት በሚደረገው ሂደት ሁሉ የበኩሉን ሚና የሚጫወት ይሆናል። ይህን ተፈላጊ ተቋም የራሱ የገቢ ምንጭ የመፍጠር አቅም የሚኖረው እንደሚሆን ክቡር ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል መናገራቸዉን አዲስ ማልዳ ከኤጀንሲዉ ባገኘችዉ መረጃ ማወቅ ተችሏል።
አዲስ የሚቋቋመዉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት በሙያ ማህበራቱ አመራርነት በ2014 ወደ ስራ እንደሚገባ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታረቀኝ ገረሱ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



