የጎዳና ተዳዳሪዎች በ2013ቱ አገራዊ ምርጫ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያሥችሉ ስራዎች አለመስራቱን የምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ኃላፊዋ በተለያዩ አገራችን ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎች በምርጫዉ እነዲሳተፉ የሚያስችል ስራ መስራቱን ገልጸው፣ በተለየ መለኩ ኑራቸዉን በጎዳና ላይ ያደረጉ በርካታ ዜጎች የሚመርጡበትን መንገድ አለማመቻቸቱን አስታዉቀዋል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ በነበሩ ተሞክሮዎች ላይ አዲስ ማለዳ ባደረገችዉ ዳሰሳ፣ እነዚህ ዜጎች በተደራጀና በልዩ መልኩ በምርጫ የሚሳተፉበት ተግባር ምርጫ ቦርድ አለመስራቱን ለማወቅ ችላለች። ኃላፊዋም ኑሯቸዉን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ስሌላቸዉ በምርጫ ለመሳተፍ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸዉ ገልጸዉ፣ ነገር ግን የመራጮች ህግን የሚያሟላ ማንኛውም ዜጋ መምረጥ እንደሚችል አውስተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩና እድሜያቸዉ ከ18 አመት በላይ የሆኑ እና እራሳቸዉን በትክክል መግለጽ የሚችሉ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎች፣ ሀሳባቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል “መጥቶ ስለ ምርጫ የጠየቀን ፣እንደ ዜጋም የሚያየን የለም። የተመቻቸልን ነገር ካገኘን መምረጥና መመረጥ እንፈልጋልን። የምንመርጥበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከዚህ አስከፊ ህይወት የምንላቀቅበትንም መንገድ መንግሥት ቢያመቻችልን” ሲሉ አስታዉቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የሴቶችና ህጻናት እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስተር፣ “የእኛ ስራ ከጎዳና ላይ የሚነሱበትንና በዘላቂነት የሚደራጁበትን መንገድ ማመቻቸት ነዉ ፤ ይሄ ጉዳይ የሚመለከተዉ ምርጫ ቦርድን ነዉ” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች በ2010 ከዘጠኝ ክልሎች በሚገኙ 11 የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ባስጠናዉ ጥናት 88690 የሚጠጉ ዜጎች በተለያዩ ችግሮች ዉስጥ ሆነዉ ኑራቸዉን በጎዳና ላይ የሚገፉ ሲሆን፣ ከዚህ ዉስጥ አዲስ አበባ ብቻ 55000 ቁጥር ያላቸዉ ዜጎች ኑራቸዉን በጎዳና ላይ እንደሚገፉ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያ እና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፈለቀ ጀምበሬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የጎዳና ተዳዳሪዎች ምንም እነኳን ኑራቸዉን ጎዳና ላይ ቢያደርጉም ዜጋ ናቸዉ። እንደ ዜጋ ደግሞ የሚመርጡበትና ስለ ምርጫ መረጃ እንዲኖራቸዉ ምርጫ ቦርድ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግስትም በማንቃት እነዲሣተፉ የማድረግ ተግባር ሊያከናውኑ ይገባል። የሚመለከታቸው አካላት ጎዳና ላይ ያሉ ዜጎች ድምፅ እንዳይባክን አለኝታነታቸዉን ቢያሳዩ፣ እነዚህ ዜጎች ባይመርጡ እንኳን የመመረጥና የመምረጥ መብት እንዳላቸው ቢያውቁ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል፤ በዚህም እነዚህ ዜጎች የተሻለ ነገር የሚሰራላቸዉን መሪያቸዉን ሊመርጡ ይችላሉ። አዲስ ማለዳም በዚህ ላይ በትኩረት መስራቷ ትክክል ነዉ ሲሉ የማህበራዊ ባለሙያ እና የሞሽን የማማከርና ስልጠና ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ብርሀኑ ራቦ ገልጸዋል።
መመረጥም ሆነ መምረጥ ህገ-መንግሰታዊ መብት ነው።ዜጎች የመራጭነት መመዘኛዎችን ካሟሉ ደግሞ መምረጥ ይችላሉ፤ ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የህግ ባለ ሙያዉ መታገሥ ዉለታዉ ገለጹ። በልዩ ሁኔታ የሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ላይ በሚመለከት በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 17/1 እና2 እንዲሁም በአንቀጽ 18 በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ ምርጫ ቦርድ እነዚህ ዜጎች የመብታቸዉ ተጠቃሚ እነዲሆኑ ማድረግ ይችላል ሲሉ የህግ ባሉሙያዉ አክለው ገልጸዋል።
የሕግ ባለሙያዉ አያይዘዉም ኑራቸዉን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ከየትኛዉም ሕብረተሰብ በላይ መሰረታዊ ጥያቄዎች ያሉባቸዉ ዜጎች እንደመሆናቸዉ የሚመርጡበት መንገድ ቢመቻችላቸዉ ሲሉ አስተያታቸውን ሰጠተዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



