የሰላም ሚኒስቴር ከኹለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር የምክክር መድረክ ካካሄደ በኋላ ግጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአገርና የግለሰቦች ንብረትም መውደሙን እንዲሁም ብዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች መከሰታቸውን የሶማሌ ክልል የመስተዳድሩ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ መሐመድ ሮብሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስቴር መጋቢት 30/2013 በአፋርና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተፈጠሩትን ግጭቶች ለማስቆም፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር እና በኹለቱ ክልሎች ለተከሰተው ግጭት አፋጣኝ መፍትሔ ለማበጀት፣ ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድና የልዑካን ቡድኖቻቸው፣ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት የሰላምና የፀጥታ መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር ማድረጉ ይታወሳል።
በሁለቱ ክልሎች ተከስቶ በቆየው ግጭት ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ወደ አጎራባች ክልሎች ተፈናቅለው የሄዱ ነዋሪዎችን መልሶ ማቋቋም ስላልተቻለ ነዋሪዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ሲሉ መሐመድ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ገርበ ኢሴ የተባለቸው አዋሽ መስመር ላይ የምትገኘው ከተማ በአፋር ልዩ ሀይል ፖሊስ በመከበቧ ለተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ መቸገራውን መሐመድ ጠቁመዋል።
የሶማሌ ክልል ግጭቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ፣ በክልሉ የሚደርሰውን ሞትና መፈናቀል ለመከላከል ሲባል ተገቢውን ዕርምጃ ይወስዳል ተብሏል።
የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የአስተዳደር ወሰን የገባኛል በሚያነሱባቸው ቀበሌዎች ሊያቋቁማቸው የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ውሳኔውን የሶማሌ ክልል እንዳልተቀበለውና በምርጫ እስካለመሳተፍ የሚደርስ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደሚገደድ ማስታወቁ ይታወሳል።
የሶማሌ ክልል ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ቅሬታ እና የቦርዱ ውሳኔ እንዳለ ሁኖ አሁን ላይ የምርጫ ቅስቀሳዎች እና ምዝገባዎች በተገቢው መልኩ እየተካሄዱ እንደሆነ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረው ግጭት እየተካረረና እየተባባሳ ቢመጣም ሶማሌ ክልል የምርጫ ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የአስተዳደር ጥያቄ በሚያነሱባቸው ስምንት ቀበሌዎች የሚቋቋሙ 30 የምርጫ ጣቢያዎች በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያ ሥር ተካለው በምርጫ ቦርድ ይፋ ቢደረጉም፣ የአፋር ክልል ለቦርዱ ባቀረበው ቅሬታ ምክንያት ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎቹ እንዳይቋቋሙ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።
የአፋር እና የሶማሌ ሕዝቦች ለረዥም አመታት የተፈጥሮ ሐብቶችን ለመቆጣጠር በሚደረግ ፉክክር፣ በግዛት ይገባኛል ውዝግብ፣ እና መደበኛ ባልሆነውን የንግድ ልውውጥ የበላይነት ለማግኘት በሚደረግ ፍትጊያ በተደጋጋሚ ሲጋጩ የኖሩ መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በአፋር እና በሶማሌ መካከል ለረዥም አመታት የዘለቀው ግጭት የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደረገ ይሁን እንጂ ታሪክ፣ የወሰን አከላለል እና ፖለቲካ የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምሁራን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች መካከል በተለያዩ ወቅቶች እያደር የሚያገረሸውን ግጭት በዘለቄታው ለመፍታት ይበጃሉ ያላቸውን ውይይቶች እና ስምምነቶች ቢያካሒድም ጉዳዩ ይበልጥ እየተወሳሰበ መጥቷል።
የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች በታኅሳስ 2007 በደረሱበት ስምምነት መሰረት በተደጋጋሚ የግጭት መንስኤ የነበሩትን ገዳማይቱ፣ እንዱፎ እና አዳይቱ የተባሉት ቀበሌዎች በአፋር ክልል ስር እንዲካተቱ በፊርማ ጭምር ተረካክበው እነደነበር ይታወሳል።
የሶማሌ ክልል መንግሥት በ93 ወረዳ፣ በ11 ዞኖችና በ6 የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ መሆኑ ይታወቃል።
በአፋር ክልል ለ6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በ1ሺህ 432 ጣቢያዎች የመራጮች ምዘገባ እየተካሄደ መሆኑን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አፋር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም።
የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምክንያቶች ከተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ዘግይቶ ተጀምሯል። ከጸጥታ፣ ትራንስፖርትና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ ወደ ምርጫ ጣቢዎች መድረስ ባለመቻላቸው የመራጮች ምዘገባ የምርጫ ቦርድ ካስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ዘግይቶ መጀመሩን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቦርዱ ከመንግስት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት በክልሉ በተቋቋሙ ጣቢያዎች አስፈላጊ ቅጾች ተሟልተው ካለፈው አርብ ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



