ከሚያዝያ30/2013 በኋላ ከገንዘብ ሚንስትር ወይም ከጉምሩክ ኮሚሽን ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ የክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች ምንም አይነት ከጉምሩክ ነጻ ቀረጥ ማበረታቻ አገልግሎት እንደማይሰጡ ተናገሩ፡፡ የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ከገንዘብ ሚኒስትር በደረሰዉ ደብዳቤ መሰረት ለክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የአግልግሎት እገዳዉን ደብዳቤ እንደጻፈ ያሳወቀ ሲሆን፣ በቀጣይም ችግሩን ለመፍታት ከኮሚሽኑ ጋር እንደሚነጋገሩ ይፋ አድርጓል፡፡
አዲስማለዳ ያነጋገረቻቸዉ በአማራ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ትግስት አብረሀም፣ የክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች በተጻፈላቸዉ ደብዳቤ መሰረት እስከ ሚያዝያ 30 በዉክልና ሲሰሩ መቆየታቸዉን ገልጸዋል፡፡
ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ እቃዎችን በተመለከተ በተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን የተሰጠዉ ለገንዘብ ሚንስትር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ለአሰራር ቅልጥፍና እንዲመቸዉ በየክልሉ ለሚገኙ የገንዘብ ሚኒስተር ተቋማት ሊያወረድ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
በፊት በነበረው አሰራር ገንዘብ ሚኒስተር ለጉምሩክ ኮሚሽን አስተላልፎ ሲሰራ ቆይቶ እንደነበር አስታዉሰዉ፣ ከ2008 ጀምሮ ግን ወደ ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ እንደወረደ ተናግረዋል፡፡ የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎችም ዋነኛ ስራቸዉ ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባላሀብቶችን ብቻ ማስተናገድ እንደነበር አስታዉቀዋል፡፡
ገንዘብ ሚኒስትር በዉክልና ለክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የሰጠዉን ዉክልና ከሚያዝያ 30 በኋላ ማንሳቱን ተከትሎ አገልግሎቱን ማቋረጣቸዉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከሚያዝያ 30 በኋላ ባለሀብቶች እንዴት መስተናገድ አንደሚኖርባቸዉ አቅጣጫ አላስቀመጠም፡፡ ችግሩ እንዲቀረፍ የፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸዉን እና ጠብቁ መባላቸዉን አስታዉቀዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከጉምሩክ ነጻ ቀረጥ የሚያሥገቡ ባላሀብቶች እቃዎቻቸዉ ጉምሩክ ላይ በቆየ ቁጥር የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን እንደሚጨምርባቸዉና ኢንቨስትመንታቸዉም ላይ መጓተትን እንደሚፈጥርባቸዉ ሀላፊዋ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዉ ባለሀብት ከሚያዝያ 30 በኋላ በክልል እንደማይሥተናገዱ ቢያዉቁም መረጃዉ የሌላቸዉም አሉ ተብሏል፡፡ በአዋጁ መሰረት ገንዘብ ሚኒስተር ከቀረጥ ነጻ ከፈቀደ በኋላ ወደ ጉምሩክ ኮሚሽን ባለሀብቶቹ ሄደዉ ሊስተናገዱ ይችላሉ ተብላል፡፡ ባለሀብቶች መረጃዉ እንዲደርሳቸዉ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ባሉበት እንዲቆዩ መልዕክት በማስተላለፋቸዉ ችግሩ በቅርቡ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ በገንዘብ ሚንስትር የታክስ ፖሊሲ ዳሬክተር ሙላይ ወልዱ በበኩላቸዉ፣ የክልል እና የፌደራል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የባለሀብቶችን ጥያቄ በማጣራት ብቁ የሆኑትን ለገንዘብ ሚኒስተር ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ የክልል አገልግሎትም እንዲቀጥል ይፈለጋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ባለሀብቶችም በክልል ባሉበት ቦታ(online) ሆነዉ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ቢሆንም፣ እስካሁን በቀጥታ የገቡት የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ብቻ ተጠቃሚ መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡
በቀጥታ(oniline) ያልገቡትን ክልል ባለሀብቶችን ወደ አሰራሩ እዲቀላቀሉ እስከ ሁለት ወር ድረስ ጊዜ እንደሚሰጣቸዉና እስከዛዉ በነበረዉ የክልል አሰራር እንዲቀጥል ነዉ ብለዋል፡፡
ክልሎች ከሚያዝያ 30 በፊት ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ማበረታቻ ተጠቃሚ ባለሀብቶችን ተቀብለዉ እና አጣርተዉ ለጉምሩክ ኮሚሽን ይልኩ የነበረዉን አሁን ላይ በቀጥታ ወደ ገንዘብ ሚንስተር እንዲልኩ መደረጉም ተገልጻል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን ለባለሀብቶች የሚፈቅደዉና የሚከለክለዉ ነገር እንደሌለም በገንዘብ ሚኒስተር የታክስ ፖሊሲ ዳሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የባለሀብቶችን መረጃ ለፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ሳይሆን በቀጥታ በአዋጅ ስልጣን ወደ ተሰጠዉ ገንዘብ ሚኒስተር እንዲልኩ መታሰቡንም አስታዉቀዋል፡፡
ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻ ለባለሀብቶች መንግስት የፈቀደበት ዋና አላማዉ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና የቴክኖሎጂም ልዉዉጥ እንዲኖር ፣ እንዲሁም የስራ እድል እንዲፈጥር ታስቦ እንደሆነ ሙላይ ወልዱ ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ አሰራር ባላሀብቶች ሳይጉላሉ ቶሎ ወደ ተግባር ለመግባት በዉይይት ላይም መሆናቸዉን ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት በገንዘብ ሚኒስተር የታክስ ፖሊሲ ዳሬክተሩ ሙላይ ወልዱ አስታዉቀዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013


