ስደተኞችን በረሃ ላይ ሲያሰቃይ የቆየው ኤርትራዊ በአምስት ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባለ

ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሲያጓጉዝ፣ገንዘብ ሲቀበል እና ሴቶችን ሲደፍር የቆየው ተወልደ ጎይቶም ወይንም በቅፅል ስሙ ዋሊድ የተባለው ኤርትራዊ በተከሰሰበት አምስት ክሶች ጥፋተኛ ተባለ፡፡ ከሶስት ተከሳሾች መካከል ዋሊድ የተባለው ግለሰብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 20ኛው ምድብ በዋለው ችሎት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ 909/2015 በአንቀጽ 3(ሐ) መሰረት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኘው ዋሊድ የፍርድ ቅጣቱ የሚሰጥበት ቀን ለግንቦት 13/2013 ተራዝሟል። ኹለቱ ኤርትራውያን ግለሰቦች ዋሊድ እና ኪዳነ ዘካሪያስ ሀብተማርያም ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ተይዘው ለፍርድ የቀረቡ ሲሆን፣ ኪዳነ ዘካሪያስ ሀብተማርያም ከእስር ማምለጡ ይታወሳል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አሁንም ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ወደ ሊቢያ የተሰደዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ሥደተኞችን በመግደል፣ በማሰቃየት፣ በመድፈርና ሀብት በማከማቸት ወንጀል እና የሕገወጥ ሰዎች

ዝውውር ቡድን ግፍን በተመለከተ ሶስት ግለሰቦች በአንድ ወቅት ታስረው ነበረ፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንዱ በዋስ በመፈታቱና ኪዳኔ ዘካሪያስ ደግሞ ከፖሊስ እጅ በማምለጡ ምክንያት ፍርድ ቤት እየተመላለሰ የሚገኘው ጎይቶም (ዋሊድ) ብቻ ነው። ኪዳኔ ዘካሪያስ እና ተወልደ ጎይቶም ኤርትራውያን ዜጎች ሲሆኑ፣ በሊቢያ በረሃ ወደ አውሮፓ አቀናለሁ ብለው ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ የሚነሱ ስደተኞችን ጠልፈው ማጉረያ ቤት አቆይተው በማሰቃየት ከቤተሰቦቻቸው እስከ 200 ሺህ ብር እየጠየቁ፣ ብር የሌላቸውን ደግሞ በመግደል ባለፉት 5 አመታት በሚሊየን የሚቆጠር ገቢ ያገኙ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ኪዳኔ ዘካርያስ በእጆቹ ወይ በዱላ ሰው ደብድቦ መግደል ልማዱ እንደነበር በፍርድ ቤት ሲመሰከርበት የቆየ ሲሆን፣ ባልደረባው የነበረው ተወልደ ጎይቶም ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ደፍሯል ብለው የአይን እማኞች መስክረውበታል።
በሊቢያ በርሃ እንደ ኪዳኔ ጨካኝ አልነበረም የሚሉት የሟች ቤተሰቦች፣ በተለይ ቤተሰቦች ገንዘቡ የለንም በሚሉበት ወቅት ኪዳኔ ስልክ ደውሎላቸው መስመር ላይ ባሉበት የተጠለፈው ዘመዳቸው ባዶ ገላ ላይ የቀለጠ ፕላስቲክ አፍስሶ የዘመዳቸው ስቃይ በስልክ እንዲሰሙት በማድረግ ከባድ ጭንቅትና ሃዘን ውስጥ እንዲገቡ ያደርግ ነበር ብለዋል።

ተወልደና ኪዳኔ ባጠራቀሙት ሃብት ለማጎረያ ቤቶቻቸው ሊብያዊያን ዘበኞች ቀጥረው፣ መሳሪያ ያስታተቁዋቸው የራሳቸው ሚሊሻዎች የነበራቸው ሲሆን፣ በአንድ ወቅት በቁጥጥራቸው ስር እስከ 900 እስረኞችን ያለ ምግብና ውሃ በማቆየትና በማሰቃየት ወንጀል ይፈጽሙ እንደነበር የተከሰሱበት መዝገብ ያስረዳል። አርቲስት ታረቀኝ ሙሉ ከኹለቱ ተከሳሾች ጋር ጓደኝነት መስርቶ በፋይናንስ በኩል ያግዝ የነበረ ሲሆን፣ ከተጠለፉት ስደተኛ ቤተስቦች ለነ ኪዳኔ የሚተላለፍ ገንዘብ ከግብር ቆጣሪዎች በመሰወርም ይተባበራቸው እንደነበር ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መረጃ አቅርቧል።

አርቲስት ታረቀኝ “ፍቅርሽ ገብቶ በደሜ” በሚለው ነጠላ ዜማ ስሙ የተጋነነለት ቢሆንም፣ በዱባይ ኮንሰርት በሚያዘጋጅበት ወቅት ወጪውን የሚሸፈንለት የነበረው ኪዳኔ ነበር ተብሏል። ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ ሙሉ ታረቀኝ ነሐሴ ወር ላይ የታሰረው፣ በነ ኪዳኔ ክስ ምስክርነት ይሰጡ የነበሩትን በገንዘብ አባብሎ ክሱ እንዲቋረጥ ሙከራ በማድረጉ ምክንያት ነበር። ታረቀኝ ሙሉ ጓደኞቹ በሕግ እንዳይጠየቁ ባደረገው ሙከራ ለተወሰነ ጊዜ በፖሊስ ተይዞ የነበረ ሲሆን በዋስ መፈታቱ ይታወቃል። ተወልደ እና ኪዳኔ ለመስማት እጅግ በጣም የሚዘገንን ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በበርካታ የአውሮፓ መንግስታትና በኢንተርፖል እየተፈለጉ የነበሩ ቢሆንም፣ ባለፈው የካቲት ወር ኪዳኔ ከእስር ቤት ወደ አዲስ አበባው የልደታ ፍርድ ቤት በተወሰደበት ማግስት ከአሳሪዎቹ እጅ አምልጦ ጠፍቷል። እስካሁን ድረስ መድረሻው አልታወቅም። የፖሊስ ምርመራና የፍርድ ሂደት ከዓመት በላይ ጊዜ የፈጀው በዋንኛነት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንደሆነ የፌዴራል አቃቤ ሕግ አስታውቆ ነበር።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here