የኩላሊት እጥበት ሕክምና ለሚያደርጉ የኩላሊት ሕሙማን የሚታዘዘው “ሂፓሬይን” የተባለው መድኃኒት ዋጋ በፋርማሲዎች 300 ብር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ከአንድ ሺሕ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን የኩላሊት ሕሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሰለሞን አሰፋ ገልጸዋል።
የመድኃኒቱ ዋጋ ከሦስት እጥፍ በላይ የጨመረው ለኮቪድ ታካሚዎች ጭምር አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ የነገሩን ሰለሞን፣ አሁን በአገራችን የኮቪድ ጽኑ ሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የመድኃኒቱ ተፈላጊነትም በዛው ልክ በመጨመሩ ምክንያት እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎች ለሕክምናው ከሚያወጡት ገንዘብ በተጨማሪ የመድኃኒት ዋጋ መጨመሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል በማለት የኩላሊት ሕሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጁ የችግሩን አሳሳቢነት አሳውቀዋል።
ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ ጀምሮ የተለያዩ መድኃኒቶች እየጠፉ መሄዳቸው እና በሌሎች ሕመሞች በጽኑ ታሞ ወደ ሕክምና ተቋማት ሄዶ በቂ የሆነ ግልጋሎት ለማግኘት አለመቻሉ የኮቪድ ሌላኛው ፈተና እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም፣ እነዚህን የኩላሊት ሕሙማን በኮቪድ እንዳይያዙ ሕብረተሰቡ ጭምር ሊጠነቀቅላቸው ይገባል። በተለያዩ የትራንስፖርት መገልገያዎች ውስጥ እና በሌሎችም ቦታዎች ሕብረተሰቡ በአግባቡ ማስክ ማድረግ እና ሌሎች ተጓዳኝ ሕመሞች ላሉባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል በማለት አሳስበዋል።
ሂፓሬይን በመርፌ የሚሰጥ የመድኃኒት አይነት ሲሆን ከደም መርጋት ጋር ለተያያዙ ችግሮች ሕክምና የሚውል መድኃኒት መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። መድኃኒቱ በተለይ ደግሞ የደም መርጋት እንዳይከሰት እና ከተከሰተ በኋላም ለመከላከል እንደሚያግዝ ጭምር ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ በተለያዩ ሕመሞች ተዳክመው ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የገቡ ታካሚዎች ከመኝታቸው ስለማይንቀሳቀሱ ደም መርጋት እንዳይከሰት መድኃኒቱ እንደሚመከር ከባለሙያች ለመረዳት ተችሏል።
በካዲስኮ ሆስፒታል የኮቪድ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዘላለም ተስፋዬ የኮቪድ ሕመምተኞች በቶሎ ወደ ሕክምና መስጫ ተቋማት ስለማይመጡ በሽታው ያዳክማቸዋል። ደረታቸው አካባቢ የመታፈን እና የመጫን ስሜት ስለሚኖራቸው ሂፓሬን ሊወጉ ይችላሉ። ስለዚህ መድኃኒቱ ለኮቪድ ሕክምና አስፈላጊ ነው በማለት ገልጸዋል።
ዶክተር ዘላለም አክለውም፣ በቀላሉ መድኃኒቱን ለማግኘትም አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ፤ ከነማ መድኃኒት ቤቶች 400 ብር የሚሸጠው መድኃኒት በግል መድኃኒት ቤቶች ከአንድ ሺሕ ብር በላይ እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል። ኮሮና ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች አንዱ የደም መርጋት እንደሆነም አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ኹለት ሺሕ 400 ያህል የኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል 105 ያህሉ ብቻ በመንግሥት ሆስፒታሎች ሕክምናውን እንደሚያደርጉ ሰለሞን ተናግረዋል። የእነዚህ 105 ታካሚዎች ሙሉ የሕክምና ወጪ በመንግሥት የሚሸፈን ሲሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የምስጋና ቀንን ምክንያት በማድረግ የዘውዲቱ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት ቃል በገቡት መሰረት በ 2013 የበጀት ዓመት የሕክምና ወጪያቸው በመሸፈን ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰለሞን አክለውም፣ የኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚያደርጉ የግል ሆስፒታሎች ከ500 እስከ አንድ ሺሕ ብር ድረስ ጭማሪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚያደርጉ ሰዎች በየኹለት ቀናት ወደ ሕክምና መስጫ ሥፍራዎች ለህክምናው ስለሚያመሩ ከከፍተኛ ወጪው ባሻገር ኮሮናን ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው ብለዋል። አሁን ያለው የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የተለያዩ ባለሀብቶች ድጋፍ አድርገውላቸው ይታከሙ የነበሩ ታካሚዎች ከባለሀብቶቹ የሚያገኙትን ድጋፍ በማጣታቸው ችግር ላይ ወድቀዋልም ብለዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013



