በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የበይነ መረብ (በኦንላይን) የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት የሚሰጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ። የኦንላይን ትምህርት ፈቃድ ያገኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ “ላይፍ ማፕ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም” ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ መግባቱን የላይፍ ማፕ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፕሬዝዳንት ታዬ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ተቋሙ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ፈቃድ ማግኘቱን የገለጹት የተቋሙ ፕሬዝዳንት፣ እስካሁን ከነበረው የትምህርት አሰጣጥ በአዲስ መልክ የመጣ የትምህርት ስልት ነው ብለዋል። ላይፍ ማፕ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከኤንጀሲው ፈቃድ ያገኘው በቅርቡ መሆኑን የጠቆሙት ታዬ፣ ፈቃዱን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በማኔጅመንት፣ አካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በኦንላይን ለመስጠት በመመዝገብ ላይ ነው ተብሏል።
ትምህርቱ የሚሰጠው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ሲሆን፣ የመማሪያ ሞጁሎች፣ የድምጽ፣ የምስል መማሪያ እና ፈተናን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚጠናቀቁ የትምህርት ሂደቶችን እንደሚከተል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል። ተቋሙ ይህን የኦንላይን ትምህርት በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላቱ ተነግሯል። ላይፍ ማፕ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለአንድ ክሬዲት ሀወር 250 ብር እንደሚያስከፍል ነው ፕሬዚደንቱ የገለጹት። ይሁን እንጅ እንደየ ትምህርት አይነቱ የክፍያ መጠኑ እንደሚለያይ ነው የተገለጸው። የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታረቀኝ ገረሱ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ ላይፍ ማፕ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በኦንላይን የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
ተቋሙ ፈቃዱን ያገኘው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የበይነ መረብ ትምህርት(ኦንላይን ትምህርት) የከፍተኛ ትምህርት እውቅና ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያን መሰረት አድርጎ መሆኑን ታረቀኝ ጠቁመዋል። የኤጄንሲው ተግባር ጥያቄ የሚያቀርቡ ተቋማት ያቀረቡትን ጥያቄ በመመሪያው መሰረት ማሟላት ያለበትን ማሟላቱን በመገምገም ፈቃድ መስጠት መሆኑን አስታውሰዋል። በዚሁ መሰረት ኤጀንሲው የላይፍ ማፕ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈቃድ የተሰጠው በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን ዝርዝር መስፈርቶች እንደ ግብዓትና የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ማሟላቱን ኤጀንሲው በማረጋገጡ ነው ተብሏል።
ከዚህ በፊት የነበረው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አሰጣጥ የርቅት ትምህርትና መደበኛ ብቻ መሆኑን ያስታወሱት ታረቀኝ፣ የኦንላይን ትምህርት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል። ይህም በትምህርቱ ዘርፍ የተማሪዎች የትምህርት እድል አማራጭ እንዲሰፋና በመደበኛና በርቅት ትምህርት ለመማር የማይችሉ ተማሪዎችን ለማሳተፍ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የበይነ መረብ ትምህርት(ኦንላይን ትምህርት) ዘግይቶ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት ታረቀኝ፣ በመደበኛ ትምህርት ለመሳተፍ ሁኔታዎች የማይፈቅዱላቸው ተማሪዎች ወደ ሕገ ወጥ ተግባራት እንደሚያመሩ ጠቁመዋል። በኦንላይን ትምህርት አማካይነት ወደ ሕገ ወጥ የትምህርት ሥርዓት ይገቡ የነበሩ ተማሪዎችን ማሳተፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ከመደበኛ እና ከርቀት ትምህርት በተሻለ ሁኔታ መከታተል ያስችላል ተብሎለታል።
ተማሪዎች ተቋማት ከኤጀንሲው እውቅና ያገኙበትን ማስረጃ በማረጋገጥ እንዲገለገሉ ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎች በኦንላይን ትምህርት እንሰጣለን በማለት የሚያጭበረብሩ ተቋማት ሊኖሩ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013



