ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ለተጨማሪ ኹለት ዓመታት ተጓተተ

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ 20 ሚሊየን ዶላር ለዚህ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ከመንግሥት ተመድቧል

በአማራ ክልል ደጀን ወረዳ ላይ ከኹለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኹለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ቢገለጽም፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ማሽነሪዎቹ ቀድመው ባለመመረታቸው ግንባታው ለተጨማሪ ኹለት ዓመታት መጓተቱ ታውቋል።

የሲሚንቶ እና ሌሎች ተዛማጅ ኢንደስትሪ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ልማት ዳይሬክተር ስመኝ ደጉ ግንባታው በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደተጓተተ ገልጸው፣ ካለፈው መስከረም ወር 2013 ጀምሮ የግንባታው እቅድ እንደገና ታድሶ በቀጣይ ኹለት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አዲስ እቅድ መነደፉን ተናግረው፣ ፕሮጀክቱ መጓተቱ ለተጨማሪ ወጭ እንደሚዳርግም አሳውቀዋል።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ 20 ሚሊየን ዶላር ለዚህ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መመደቡን ያስታወሱት ስመኝ፣ መንግሥት በገጠመው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ፋብሪካው ግዙፍ የአገር ፕሮጀክት ቢሆንም እንደ መድኃኒትና ማዳበሪያ ላሉት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባ ፕሮጀክቱ ተጓቷል ብለዋል።

በዚህ በጀት ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ የግንባታ ደረጃ ላይ ማለትም የመሬት ዝግጂት ሥራዎች ላይ እንደሆነ እና የማሽነሪ ቅድመ ክፍያ እንደተከፈለ ገልጸው የመሬት ቁፋሮ ፣የሠራተኞች መኖሪያ፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር በአማራ ክልል ደጀን ከተማ ላይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ከኹለት የውጭ አገር ድርጅቶች ጋር የሦስትዮሽ የሥራ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ግንባታው በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ እና በ8 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት እንደሚሠራ መገለጹ ይታወሳል።

አክስዮን ማኅበሩ በወቅቱ ስምምነቱን የተፈራረመው መቀመጫውን በዴንማርክ ኮፐንሃገን ካደረገው ዓለም አቀፍ የምህንድስና ኩባንያ ከሆነው “FLSmidth & Co. A/S” እና መቀመጫውን ቻይና ካደረገው ሌላው ዓለምአቀፍ የምህንድስና ኩባንያ “Hengyuan Group” በጋራ በመሆን ነው።

በስምምነቱ መሠረት “FLSmidth &Co. A/S” የግንባታ መሣሪያዎችን ሲያቀርብ፣ “Hengyuan Group” የግንባታውን ሥራ እንዲያከናውን ነበር። የፋብሪካው ግንባታ አጠቃላይ ወጪውም 8.8 ቢልዮን ብር እንደሆነና ግንባታው በ2 አመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ስምምነቱ በተፈረመት ጊዜ ተገልጿል።

በ123 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ በቀን 7 ሺሕ 500፣ በዓመት ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከረጢት ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ነው ተብሏል። ለዚህም 655 ሰዎችን በቋሚነት የሚቀጥር ሲሆን፣ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ደግሞ የሠራተኞቹን ቁጥር ወደ 1 ሺሕ 500 ለማሳደግ እንደታቀደ በግንባታው ስምምነት ጂማሮ ላይ መነገሩ ይታወሳል።

ደጀን ወረዳ በአማራ ክልል ለሲሚንቶ ፋብሪካ የሚሆኑ ሁሉም የማዕድን አይነቶች በቅርብ ርቀት ከሚገኙባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተገልጿል። ዓባይ አክሲዮን ማኅበር አመቺነቱን በጥናት አረጋግጦ የግንባታ ቦታውን መምረጡን አስታውቋል። እንደ ላይምስቶን፣ ጅብሰም፣ ቀይ አፈር (ክለይ) እና ሲልካ ማዕድናት በዓባይ በርሃ አካባቢዎች በስፋት ይገኛሉ። ኢንዱስትሪው ደጀን ላይ እንዲገነባም ቀዳሚ ምክንያት ነው ተብሏል።

የዓባይ የሲሚንቶ ፋብሪካ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አስራት ኪዳኑ ፋብሪካው መጀመሪያ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አሁን ባለበት ሂደት ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ እና ፕሮጀክቱ ከኹለት ዓመት በፊት ሲፈረም በተያዘለት የግንባታ በጀት እየተሠራ እንዳለም አሳውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here