የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የአካባቢ ንጽህናንና የጤና አገልግሎት ላይ ያተኮሩ 36 አገር አቀፍ የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት ረቂቅ ደረጃ ማዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ያዘጋጃቸው 36 የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት ረቂቅ ደረጃዎች ከዚህ በፊት ያልነበሩና አዲስ መሆናቸው ተገልጿል። አዲስ የተዘጋጁት ረቂቅ ደረጃዎች መሰረታቸውን አገር አቀፍ የንጽህና እና የአካባቢ ጤና ላይ ያደረጉ ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ያዘጋጃቸው ረቂቅ ደረጃዎች በኹለት እንደሚከፈሉ የኤጀንሲው የአካባቢ፣ የጤናና ደህንነት ደረጃዎች ዝግጅት ባለሙያ ደሳለኝ እሸቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የመጀመሪያው ጤና ነክ ተቋማት፣ ኹለተኛው ደግሞ የማኅበራዊ ተቋማት ደረጃዎች መሆናቸውን ደሳለኝ አብራርተዋል።
በጤና ነክ ተቋማት ሥር የሚካተቱ ደረጃዎች በቀጥታ ከጤና ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ከተዘጋጁት ረቂቅ ደረጃዎች መካከል ሆስፒታል፣ ጤና ጣቢያ፣ ስፔሻላይዝድ ክሊኒክና ሌሎችም ከጤና ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ተብሏል።
እንዲሁም ጤና ነክ ተብለው በጤና ሥር የሚካተቱ እንደ ቁርስ ቤት፣ የጀበና ቡና፣ ሆቴል፣ ባርና ሬስቶራንትና የባህል ምሽት ቤቶች እንደሚገኙበት ደሳለኝ ገልጸዋል። ጤና ነክ የሚባሉት በሚሰሩት ሥራ ምክንያት መስፈርቱን ባለማሟላታቸው በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ መሆናቸው ተግልጿል። ማኅበራዊ ተቋማት ሥር የሚካተቱት ደግሞ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የአረጋውያን ማቆያዎች፣ ማረሚያ ቤቶችና የስደተኞች መጠለያ ናቸው ተብሏል።
ጤናና ልማት በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን የሚገልጸው ኤጀንሲው፣ በጤናና ልማት ወደ ኋላ መቅረት ለበርካታ የጤና ችግሮች ሕብረተሰቡን እንደሚያጋልጥ ይገልጻል። በአብዛኛው ለችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎች በግለስብና በኅብረተሰብ የአኗኗር ዘይቤና ባህርይ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሚሆኑ ተመላክቷል።
በዚሁ መሰረት የአካባቢና ጤና አጠባበቅን በሚገባ በማጠናከር እነዚህን በሽታዎች በመጠኑም ቢሆን መከላከል እንደሚቻል ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጤና ሚኒስቴር የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት ረቂቅ ደረጃ ዝግጅት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
ረቂቅ ደረጃው ጸድቆ ሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት ሕብረተሰቡን ከተላላፊ በሽታዎች በመታደግ አላስፈላጊ የህክምና ወጪን ከማዳኑ ባሻገር፣ ጤናማ ሕብረተሰብን ከመፍጠር አንፃር ሚናው የጎላ እንደሚሆን ደሳለኝ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በጤናና በማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች ከመሙላት ባሻገር፣ ጤናማ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሏል። በማኅበራዊ ተቋማት በኩል የሚታዩ የአገልግሎት ጥራትና እርካታ ክፍተቶችን ለመሙላት በዝግጅት ላይ የሚገኙት ረቂቅ ደረጃዎች ሚናቸው የጎላ እንደሚሆን ተመላክቷል።
በዚህ ረቂቅ ደረጃ ዝግጅት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከክልል ጤና ቢሮዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እንደተሳተፉበት ደሳለኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ 142 ጤና ተቋማት እንዳሉ የጠቆሙት ደሳለኝ፣ ቀሪዎቹ ደረጃ ያልተዘጋጀላቸው የጤና ተቋማት በቀጣይ ደረጃ እንደሚዘጋጅላቸው ጠቁመዋል። በረቂቅ ዝግጅት ላይ የሚገኙ ደረጃዎች ተጠናቀው ከጸደቁ በኋላ የትግበራ አፈጻጸም ጥናት እንደሚካሄድባቸው ተጠቁሟል።
ኤጀንሲው ከዚህ በፊት ያዘጋጃቸወን የተለያዩ ደረጃዎች፣ ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ማጽደቁ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ደረጃዎችን እንዲያጸድቅ ሥልጣን ለተሰጠው የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በሥድስት ዘርፎች ተዘጋጅተው በቀረቡለት 289 ረቂቅ ደረጃዎችን ላይ በመወያያት 285ቱ ደረጃዎች ብሔራዊ ደረጃዎች እንዲሆኑ ወስኗል። ከጸደቁት ደረጃዎች ውስጥ 148 አዲስ ሲሆኑ፣ 44 ደረጃዎች የተከለሱ፣ 93 ደረጃዎች እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ በድምሩ 285 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አጽድቋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013



