የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ፈተና አሰጣጡ ወዝግብ አስነሳ

0
1750

ከማንኛዉም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚጨርስ የጤና ተመራቂ ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ(ሄርካ) ማረጋገጫ ካልተሰጠዉ በቀር የሙያ ብቃት ምዘና መፈተን እንደማይችል እየታወቀ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ምዘናዉን እንዲወስዱ አድርጓል ሲል ኤጀንሲዉ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቋል።

ኤጀንሲዉ መጋቢት 10/2013 ለጤና ጥበቃ ፣ለክልል እና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች በላከዉ ደብዳቤ የተመራቂ ተማሪዎችን ዝርዝር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀብለዉ የብቃት ምዘና እንዳይሰጡ አሳስቦ እንደነበርም አስታዉሷል።

ሆኖም ግን የክልል ጤና ቢሮና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኤጀንሲዉን አሰራር ባልተከተለ መልኩ ፈተናዉን ለመሥጠት ተዘጋጅተናል በሚል ምዘናዉን አከናዉነዋል።
ማንኛዉም ከግል ተቋም በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ደረጃ የተመረቀ ተማሪ የተማረበት ተቋምና የትምህርት መስኩ ከእዉቅና ፍቃድ ጀምሮ ሕጋዊነቱ በኤጀንሲዉ መረጋገጥ እንደሚኖርበት አመላክቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በበኩሉ ለከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲየተፈታኞችን ዝርዝር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቀዉም ሊልክልን ባለመቻሉ በቀጥታ ለትምህርት ተቋማት ደብዳቤ በመጻፍ የሚያስመረቋቸዉን የጤና ተማሪዎች ዝርዝር እንዲልኩልን አድርገናል ብሏል።

ከ2008 ጀምሮ ከኤጀንሲዉ ትክክለኛ የተማሪዎችን ቁጥር ለማግኘት ስላልቻልን ከዛ ጊዜ ጀምሮ ጤና ጥበቃ የሙያ ብቃት ምዘና የሚወሰወዱ ተማሪዎችን ዝርዝር እና መረጃዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመዉሰድ ምዘናዉን ሲሰጥ መቆየቱም ተገልጿል።

በቅርቡ ግን ኤጀንሲዉ ለጤና ጥበቃ በጻፈው ደብዳቤ በሄርካ እዉቅና ያልተሰጣቸዉን ምሩቃን የሙያ የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ፈተና እንዳትሰጡ ሲል አሳስቦ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከጤና ጥበቃ ሚኒስተር ያገኘችዉ መረጃ አመላክቷል።

አሁን ላይ የኤጀንሲዉ ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም ከዚህ በፊት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ኤጀንሲዉ ባለመመለሱ ከየትምህርት ተቋማቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
ምሩቃን የብቃት ምዘና ፈተና ከመዉሰዳቸዉ በፊት በመጀመሪያ የትምህርት ማስረጃዎቻቸዉን የማጣራትና ወደ ጤና ጥበቃ የመላክ ሥራና ስልጣን የሄርካ መሆኑንም ጤና ጥበቃ አስታዉቋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የምዘና ፈተናዉን ከመስጠቱ በፊት ከሕግ አግባብና አሰራር ዉጪ ተምረዉ ከተገኙ ዉጤታቸዉ ሊያዝላቸዉ እንደማይችል በኤ.ቲቪ እና በሬዲዮ ለተፈታኞች ማስታወቂያ ማስነገሩን አስታዉሷል። ከዚህም በተጨማሪ የግል እና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ወደ ሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ከመግባታቸዉ በፊት አጭር ገለጻ ተደርጎላቸዉ እንደነበረም ተነግሯል።
ምዘናዉ ከተሰጠ በኃላ ግን ሄርካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተፈታኞችን የትምህርት ማስረጃቸዉን ማጣራት እፈልጋለሁ ሲል ጥያቄ ማንሳቱን ጤና ጥበቃ ይገልጻል።

መጋቢት 21/2013 በጤና ሚኒስቴር አማካይነት ከመንግሥት እና ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተዉጣጡ 17159 ምሩቃን የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ፈተና መዉሰዳቸዉን አዲስ ማለዳ ከጤና ሚኒስቴር ባገኘችዉ መረጃ ለማወቅ ችላለች።

በጥያቄዉ መሰረትም ምዘናዉን ያለፉ ከግል ትምህርት ተቋማት 1796 ሲሆኑ የእነዚህንም ተፈታኞች ስም ዝርዝር ለኤጀንሲዉ መላኩን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ መረጃዉን አድርሷል።
አዲስ ማለዳ በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ግቢ ዉስጥ በመገኘት የሙያ ብቃት ምዘና ፈተናዉን የወሰዱ የግል ትምህርት ተቋማት ተፈታኞችን አግኝታ አነጋግራለች።
ተፈታኞቹ በበኩላቸዉ ዉጤታችንን ጤና ሚኒስቴር ኦንላይን ላይ ቢለቀዉም ሄርካ መጀመሪያ የትምህርት ማስረጃችሁን አቅርቡና ይጣራ ማለቱን አስታዉቀዋል።

አዲስ ማለዳ በኤጀንሲዉ ግቢ ዉስጥ ተሰልፈዉ ያገኘቻቸዉ የአየር ጤና፣ የሪፍት ቫሊ፣ የአይካንና የሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ምሩቃን የሙያ ብቃት ፈተናዉን ከወሰድን በኋላ ለአንድ ወር ዉጤት ስንጠብቅ ቆይተናል ብለዋል ። ኤጀንሲዉ ለምን ዉጤት እስኪወጣ ጠብቆ የትምህርት ማስረጃችሁን ላጣራ ይላል ሲሉ ቅሬታቸዉን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በር ላይ ከአርባ ምንጭ፣ ከሰላሌ ፍቼ፣ ከሐዋሳ ፣ አዳማና ከሌሎችም የአገሪቷ አካባቢዎች የመጡ በርከት ያሉ ተማሪዎችን አዲስ ማለዳ አግኝታ ያነጋገረች ሲሆን፣ ሄርካ የትምህርት ማስረጃቸዉን እንዲያጣሩ ወደ ፈተናዎች ኤጀንሲ እንደላካቸዉ ተናግረዋል። የፈተናዎች ኤጀንሲ ቀጠሮ ስለሚያሲዝ ከክፍለ አገር የመጡ ምሩቃን ለአልጋና ለምግብ ወጪ መዳረጋቸዉን ተናግረዋል።

ሄርካ በበኩሉ ተፈታኞች ዉጤታቸዉን ማየት የሚችሉት የትምህረት ማስረጃቸዉን ትክክለኛነቱን ካረጋገጥኩኝ በኃላ ነዉ ማለቱን የኤጀንሲዉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ታረቀኝ ገረሱ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here