ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር (ታኮን) ከተለያዩ የመንግሥትና የግል አበዳሪ ተቋማት፣ የህንፃ መሳሪያ አቅራቢዎች እንዲሁም ከተቋሙ ሠራተኞች የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀቶች እንደተላከላቸው አዲስ ማለዳ በተቋሙ ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ መረዳት ተችሏል።
ድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ የተለያዩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ባደረሱት መረጃ መሠረት ከ2012 መጨረሻ አካባቢ ተቋሙ ውስጥ ችግሮች ሲታዩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በታኮን ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ለበርካታ ወራት ደሞዝ ሳይከፈላቸው ከሥራ ገበታቸው በመፈናቀላቸው ደሞዛቸውንም ለማግኘት ከተቋሙ ጋር በመካሰስ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በችሎት ላይ ሊቀርቡልን እና የት እንዳሉ ማወቅ አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አድርሰዋል።
ተቋሙ አሁን ላይ በርካታ ሠራተኞችን ያለደሞዝ ከሥራ ገበታቸው የበተነ መሆኑንም አዲስ ማለዳ በተቋሙ ተገኝታ ያገኘችው በርካታ የክስ ወረቀቶች መሰረት ማወቅ ተችሏል።
በታኮን ሲሰሩ የቆዩ ሰራተኞች እንደሚሉት ከሆነ ተቋሙ የነበሩት መኪኖቹ ተሰብስበውና ሌሎችም ንብረቶች ተሽጠው በፍርድ ቤት ተወስኖ ደሞዝና አገልግሎት ክፍያ እንዲያገኙ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ አበዳሪ ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ አከራዮች እና እቃ አቅራቢ ድርጅቶች ተቋሙ ገንዘባቸውን ሳይከፍላቸው በመቅረቱ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት እንደደረሰው አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
የተቋሙን ንብረቶች አሁን ላይ በሃላፊነት የሚያሥተዳድር አካል አለመኖሩን እንዲሁም ተቋሙ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በጅምር በየቦታው መቆማቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የታኮን ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎች በአንዳንድ ቦታ ታርጋቸው እየተፈታ ተጥለው እንደሚገኙ ምንጮቹ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተቋሙ ለዳሽን ባንክ በእዳ ያስያዛቸውን ተሽከርካሪዎች በሐራጅ ሊሸጥ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያወጣውን ማስታወቂያ መመልክት ችላለች።
ተክለብርሀን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን)ከዳሽን ባንክ የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ለብድር ያስያዛቸውን ከ21ሚሊዮን ብር በላይ ሊያወጡ የሚችሉ 11 ተሽከርካሪዎች፤ ባንኩ በሐራጅ ቁጥር ዳባ/0011/21 በጨረታ አወዳድሮ እንደሚሸጥ ግንቦት 8/2013 በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ ከባንኩ ጋር ባደረገችው ቆይታ ኩባንያው የተበደረውን የገንዘብ መጠን ለማወቅ ሙከራ ብታደርግም ባንኩ ደንበኛቸው በሌሉበትና ሳይፈቅዱ መግለጽ እንደማይችል ተናግሯል።
ባንኩ ጨረታውን ለማውጣት ከመወሰኑ በፊት ከተቋሙ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ሙከራ ቢያደርግም ሊያናግር የሚችል የአስተዳደር አካል በማጣቱ ባንኩ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ በእዳ የተያዙትን ንብረቶች ለመሸጥ መገደዱንም ስሙ እንዲጠቀስ ያለፈለገ የባንኩ ሰራተኛ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ባንኩ ከተበዳሪው ጋር በገባው ውል መሰረት ክፍያው መከፈል ስላለበት፣ የተበደረውም የህዝብ ገንዘብ ስለሆነ በብድር የያዘውን ንብረት ባንኩ ሸጦ ገንዘቡን ለመመለስ መዘጋጀቱን ገልጿል።
አዲስ ማለዳም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወደ ታኮን ዋናው መስሪያ ቤት በማቅናት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ብትሞክርም ተቋሙ ሥራ በማቆሙ ኃላፊዎቹን ማግኘት አልቻለችም። በተቋሙ ግቢ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይም በርከት ያሉ ከተቋሙ ሰራተኞች እና ከተለያዩ የአበዳሪ ተቋማት የተላኩ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀቶች የማስታወቂያ ቦርዱን ማጨናነቃቸውን ለማወቅ ችላለች።
አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ድርጅቱ ላይ በተነሱ ጥያቄዎችና ክሶች ዙሪያ ከድርጅቱ ባለቤቶች እስከ ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊዎች ስልክ በመደወል እና ተቋሙ ድረስ በመሄድ ለማነጋገር ሞክራ አልተሳካም።
አሁን ላይ ታኮን ይገነባቸው የነበሩ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከ20 በላይ የመንግስት ተቋማት የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቋርጠው እንደሚገኙ ታውቋል። በጅምር ከቀሩት ፕሮጀክቶች መካከል የተወሰኑት አዮ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ የትግራይ ስታዲየም ግንባታ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ቅርንጫፍ ይጠቀሳሉ።
አዲስ ማለዳ ባገኘቸው መረጃ መሰረት ታኮን ከሚገነባቸው መካከል ለ13ቱ ፕሮጀክቶች ከ7.87 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሰሩ የነበሩ ቢሆንም ከቡራዩ የትምህርት ቤት ፕሮጀክት በስተቀር ሁሉም መቆማቸው ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013




በጣም ጥሩ ሚድያ ነዉ!