የዓለምን ጦርነት ወደእኛ አናምጣ!

0
641

ዓለምን ያቃወሱ ታላላቅ ጦርነቶች ተብለው በታሪክ የተመዘገቡት ኹለት ቢሆኑም ከእነሱ ቀደምም ብዙዎች ያለቁባቸው ዘግናኝ ጦርነቶች ተካሂደው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። በርካታ አገራት ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉበትና በሚሊየኖች ያለቁባቸው የቅርቦቹ 2ቱ ቢሆኑም፣ ከዛ ወዲህም ስም ያልተሰጣቸው ብዙ አገሮችን ያሳተፉ ቀዝቃዛውን ጦርነት አይነት ውጊያዎች በየጊዜው እየተካሄዱ ይገኛሉ። ዓለማችን አሁንም ጦርነትና ግድያ ሳይፈፀምባት አንድ ቀን እንደማታድርም ይነገራል። አንድ አካባቢ ሰላም ሲሆን ሌላው ይጋጫል፤ አንዱ አቅም ሲያገኝ ወዳጁን እየረዳና እየገፋ ሌላውን ይጨቁናል። አሁንም በዚህ አዙሪት ውስጥ እንገኛለን። ስለዓለም ጦርነት ማውሳታችን ሦስተኛው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቀው የዓለም ጦርነት ሊከሰት ነው ብለን ልንተነብይ ሳይሆን፣ ተመሳሳይ እልቂት ሊያስከትል የሚችል የሩቅ ጦርነትን ስበን እንዳናመጣና እንዳንቀላቀል ልናስጠነቅቅ ነው። ሠሞኑን በአይሁዳውያንና በፍልስጤማውያን መካከል እስራኤል ውስጥ እንደአዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት እየተጋጋለ በመሄዱ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው። በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉት አካላት ቁጥር እያደር በመጨመሩ የጦርነቱ አድማስ ሊስፋፋ ስለሚችል እኛ ኢትዮጵያውያን ልንጠነቀቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ኹለቱ የመካከለኛው ምስራቅ ሕዝቦች የእርስ በርስ ውጊያ የጀመሩት አሁን አይደለም። ፍልስጤማውያኑ “ኢንቲፋዳ” የሚሉትን የአመፅ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ሞክረውት ሳይሳካላቸው ቆይቷል። አይሁዳውያንም “የማያዳግም እርምጃ” እያሉ ጦርነትን በዘላቂነት የሚቋጭ ውጊያ ነው እያሉ በተደጋጋሚ መጠነ ሠፊ ዘመቻ ቢያካሂዱም እነሱም ሳይሳካላቸው፣ ተመጣታኝ ባይሆንም ከኹለቱም ወገን ብዙዎች አልቀዋል። ኹለቱ ወገኖች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ “የመሬቱ ባለቤቶች ነን” በማለት ለምድሩ ባላቸው ፍቅር ይመሳሰላሉ። ይህ ቢሆንም በጋራ የሚወዷትን አገር በማሳደግ ወይም የየራሳቸውን ግዛት በመመስረት ፋንታ አንዱ ሌላውን በማስወገድ ብቻውን ኹሉን መያዝ ይፈልጋል፤ የሌላንም ድጋፍ በየፊናው ይፈልጋል። ኹለቱም ለጥያቄያቸው ታሪካዊና ኃይማኖታዊ መሠረት በመስጠት፣ “ቦታው ይገባናል” እያሉ ፍላጎታቸውን ለዓለም ለማሳመን እሰጥ አገባ ውስጥ ከገቡ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል። ሌሎች ወዳጆቻችሁ ነን የሚሏቸው አጋሮቻቸው ለጉዳዩ የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ እነሱ የገቡበት ጉድጓድ ውስጥ ተጎትተው ይገባሉ።

ምዕራባውያን፣ በተለይም አሜሪካ፣ ከአይሁዳውያኑ ጎን በመሆን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚሰጡ ይታወቃል። በአንፃሩ እስልምና የመንግሥት ኃይማኖት የሆነባቸው ቱርክና የአረብ አገራት ከፍልስጤማውያኑ ጎን መቆማቸው ይታወቃል። የሩቅ ምስራቅ የእስያ አገራት እንዲሁም ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በይፋ የአንዱ ደጋፊ ሆነው ባይታዩም ውስጥ ውስጡን ከጥቅማቸው ጋር በተገናኘ ጎራ ለይተው እንደሚሰለፉ አያጠራጥርም።

በፍልስጤማውያንና በአይሁዳውያን መካከል ተመጣጣኝ ያልሆነ ውጊያ ሲካሄድ አሁን የመጀመሪያ ባይሆንም፣ የአሁኑን በርካታ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዩ ትኩረት ሰጥተውታል። ብዙዎች በማኀበራዊ ድረ-ገፆችና በተለያዩ መድረኮች ጉዳዩን እያነሱ ግጭቱን ሲያስተጋቡት በመቆየታቸው በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል። አንዳንዶች የቦታው ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ባለይዞታ እነእገሌ ናቸው በማለት ችግሩን ይበልጥ ከማወሳሰብ አልፈው የተለኮሰው እሳትን በማራገብ እያዛመቱት ይገኛሉ። እኛም አገር የተወሰኑ ግለሰቦች አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ወገኔ ለሚሉት ተቆርቋሪ ለመሆን በማሰብ በሚሰጡት የድጋፍ አስተያየት እሳቱን እያመጡ በመርጨት እንዳያራቡት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። የመካከለኛው ምስራቅ የተዳፈነ እሳት በተጫረ ቁጥር የረዱ መስሏቸው ፍሙን እያመጡ ማገዶ ውስጥ በመጨመር የሚወዷቸውን ከወላፈኑ ማራቅ አይችሉም። የቆየ ታሪክን መጥቀስና ማባላት ለማንም እንደማይጠቅም ከኔልሰን ማንዴላ ህይወት መማር ያስፈልገናል።

ምንም አይነት ታሪካዊም ሆነ ኃይማኖታዊ የባለቤትነት መብት የሌላቸው ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ከአህጉሪቱ ወጥታችሁ እንግሊዝ ግቡ አልተባሉም። በሀገረ እስራኤልም የትኛውም ወገን ውጣ ሳይባል በጋራ በእኩልነት ተከባብረው እንዲኖሩ ሁላችንም በጋራ መስራት እንጂ፣ በእነሱ መልክ እኛም ተሰንጥቀን ወገን መርጠን መጠዛጠዝ የለብንም።

የኹለቱ ወገኖች ግጭት ከቆመና ሰላም ከወረደ የዓለም መጨረሻ መድረሱን አመላካች ነው እስኪባል ድረስ ጥላቻቸው ከፖለቲከኞቻቸው አልፎ ሕዝቡ ጋር ደርሷል። ከእስከዛሬው ግጭታቸው የአሁኑ የሚለየው የታጠቁ ወታደሮች የሚዋጉበት ሳይሆን ሕዝብ በሕዝብ ላይ የተነሳበት፣ አንዱ ጎረቤቱን የሚያጠቃበት መሆኑ ነው። ይህ አይነት ስር የሰደደ ጥላቻ የፈጠረውን ግጭት በቀላሉ ለማስቆም አስቸጋሪ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች። እሳቱን በቶሎ ማጥፋት ወይ ማዳፈን ካልተቻለ ሌሎች እየተቀላቀሉበት ሶሪያና የመን የተከሰተው አይነት እልቂት ሊደገም ይችላል።

የእስራኤላውያኑ ግጭት ኃይማኖታዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ እምነትን መሰረት ያደረገ እገዛም ሆነ ድጋፍ መደረጉ አይቀርም። ከፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ የእስልምና እምነት ተከታይ እንደመሆናቸው እምነቱን አገራዊ ኃይማኖት ያደረጉ አገራት ከጎናቸው ቢሆኑ አይገርምም። ከ10 በመቶ በላይ ክርስቲያን ያላት ግብፅ ከአይሁዳውያኑ በተቃራኒ ብትቆምም አይገርም ይሆናል። መሰል የአይሁድ እምነት ተከታይ አጋር አገር የሌላቸው አይሁዳውያኑ ለዘመናት ሲጨፈጭፏቸው የነበሩ የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ ቢደግፏቸውም ላይደንቅ ይችላል። እኛን መሰል የተሰባጠርን ሕዝቦች ግን እንደ አገር ወገን መለየት የለብንም። የሦስቱም እምነት ተከታዮች እንደመኖራችን የሕዝብን ሀብት ለአንዱ ማዋል ተገቢ አይሆንም። ጉዳት ለደረሰበት ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ሊባል ቢችልም የራሳችንን ችግረኞች ረድተን ሳንጨርስ ሩቅ ማየት አያስፈልግም።

ጦርነትን አውግዞ ሰልፍ መውጣትና የኹለቱንም ስህተት መውቀስ ተገቢ ሊሆን ቢችልም፣ ኃይማኖታዊ ወገንተኝነትን ይዞ መደገፍና መተቸት እዛ ያለውን ጥላቻና ጽንፈኝነት ወደ አገራችን ማስመጣት ይሆናል። እስራኤላውን ከኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ እንደሆኑ በማቅረብ ‹ደግ አደረገች› እያሉ ከኢትዮጵያዊነት ሥነልቦና ያፈነገጠ አስተያየት የሚሰጡ፣ እንዲሁም ፍልስጤማውያንን በኃይማኖት መነጸር አይተው የሀማስን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የሚደግፉና ሌሎችንም የሚያንቋሽሹ ተግባራቸው ምን ሊያመጣ እንደሚችል ሊያስቡበት ይገባል። እዚሁ አገራችን ማንነትንና ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በተደጋጋሚ ሲፈጸም ሳይናገሩ ቆይተው የሩቁ ላይ ተመርኩዘው አላስፈላጊ የጥላቻ ቃላትን የሚሰነዝሩ መዘዙ በአገራችንም ውስጥ ከባድ ሊሆን እንደሚችል መረዳት አለባቸው።

ኢትዮጵያውያን ለተበደሉና ለተገፉ ከለላ በመስጠት የምንታወቅ እንጂ ለአንዱ ወግነን ሌላውን በመውጋትም ሆነ በመኮነን አይደለም። አሁን ያለነው ትውልዶች ካለፉት ተምረንና ገለልተኛ ሆነን መንፈሳዊና ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት ወይም የተሰደዱትን መቀበል እንዳለብን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። በቋፍ ያለውን የአገራችንን ሰላም ትተን የጦርነት አስመጪ ሆነን የሌላን ግብግብ ከማስተናገድ መቆጠብ አለብን። “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” እንደሚባለው የሁላችንንም ከምናሳርር ያልበሰለውን ጥሬ ብንበላ ይሻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here