የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ረቂቅ ተዘጋጀ

0
1000

የሒሳብ ሠራተኞችን (Accountant) አቅም ለመገንባት የሚያስችል አዲስ ደንብ መዘጋጀቱን በኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አበበ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ደንቡ የፈተና እና የብቃት ማረጋገጫዎችን የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት ያስችላልም ተብሏል። የሒሳብ አያያዝ ሥራ ለማንኛውም ተቋም የሚጠቅም የሙያ ዘርፍ እንደመሆኑ፣ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ የጠቆሙት አበበ ይህን የሚተገብሩ ባለሙያዎች በቂ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

ደንቡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያለውን ዝቅተኛ የኦዲት ባለሙያዎች ቁጥር እና የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎችን (IFRS) አሟልቶ ለመተግበር ይረዳል ተብሏል። በተጨማሪም በንድፈ ሐሳብ ትምህርትና በተግባራዊ አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚቋቋመው ተቋምም አስተዋጽኦ አለው ሲሉ አበበ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቦርዱ ይህንን ዓለምአቀፍ የፋይናንስ አሠራር IFRS ለመተግበር ተደራራቢ ሥራዎች፣ ማለትም ተቋማት IFRS እንዲተገብሩ የመቆጣጠር እና ባለሙያዎችን ብቁ የማድረጉን ሥራ አብሮ በመሥራቱ በተፈለገው ደረጃ እንዳይተገበር አድርጓል ሲል አበበ ነግረውናል።

ቦርዱ በአዋጅ 847/2006 ሲቋቋም ኹለት ተግባራትን አንድ ላይ ጨፍልቆ የያዘ ሲሆን፣ እነዚህም የዓለም ዐቀፍ ፋይናንሻል ሪፖርት ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የመቆጣጠር እና በዘርፉ ባለሙያዎችን ማብቃት የሚሉ ናቸው። ኹለቱን ኃላፊነቶች በአንድ ተቋም መተግበራቸው ሥራው በትክክል ተፈጻሚ እንዳይሆን አድርጎታል። ከዚህ በመነሳት ተግባራቱን በመለየት ባለሙያዎች የማብቃቱን ተግባር የሚሠራ ተቋም እንዲቋቋም ተደርጓል።

ቦርዱ ባለሙያውን የማብቃት እና የመቆጣጠር ስራ በጋራ ከሚሰራ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ እንዲሰራ በማድረግ የራሱ የሆነ የስነ ምግባር ደንብ በማዘጋጀት የሚቋቋም ነው ተብሏል። በተጨማሪም የሚቋቋመው ተቋም ባለሙያዎች ሙያውን ምን ያህል ተግባራዊ እያደረጉ ነው የሚለውን የሚቆጣጠር ይሆናል።

ተቋሙ ዓለማቀፍ የአካውንቲንግ ፌዴሬሽን የሚያወጣቸውን መስፈርቶች መሠረት በማድረግ ባለሙያዎችን የሚያበቃ ሲሆን፣ በሚሠለጥኑበት ጊዜ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እኩል ለማድረግ ይረዳል።

ኢንስትቲዩቱ ሲቋቋም የአለም አቀፍ ፌደሬሽን አባል ይሆናል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ ይቀይራል ሲሉ አበበ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በሀገራችን በሁሉም የግል፣ የመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን ቦርዱ የሚሰራ ሲሆን፣ የኢፌዲሪ መንግስት አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን መተግበር ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ በመረዳት በአዋጅ ቁጥር 847/2006 መደንገጉ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ከቦርዱ ውጪ ያሉ አማካሪዎች፣ የሚመለከታቸው ባለድረሻ አካላት መክረውበት ደንቡን ካዘጋጁ በኋላ ለቦርዱ ዳይሬክተሮች ቦርድ ቀርቦ የመጨረሻ ደረጃ ደርሷል። በቀጣይ ለሚኒስትሮች ምክርቤት የሚላክ ሲሆን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ምክንያት በትክክል መቼ እንደሚቀርብ ግን ማወቅ አልተቻለም።

በአካውኒቲንግ የተመረቁ ባለሙያዎች አጠቃላይ ተቀባይነት ያላቸው የሂሳብ አዘገጃጀት መርሆችን (GAAP) በዩኒቨርስቲ የሚሰለጥኑበት ሙያ በመሆኑ ስለ IFRS ሳያውቁ እና ሳይሰለጥኑ ወደ ስራው አለም መቀላቀላቸው እና በስራው አለም የሚጠብቃቸው አሰራር የተለያየ በመሆኑ ባለሙያዎቹ ለአዲሱ አሰራር እንግዳ ይሆናሉ ተብሏል።

የአካውንቲንግ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ60 ዓመታት በላይ ሲሆን ሙያውን ዓለም ከደረሰበት የጥራት ደራጃ ለማድረስ እና ሀገሪቱን ከአለማት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በሙያው ውስጥ ያሉ መምህራን እና ተማሪዎች ስለ IFRS ስልጠናዎች በመስጠት ለተማሪዎቻቸው አስተወፅኦ እንዲያበርክቱ እየተደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የአለማችን ሀገራት IFRSን የተቀበሉ ሲሆን ከእዚህ ውስጥ 13ቱ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸው ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here