የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት ባሳለፍነው ግንቦት 10/2013 በክልሉ በሕገወጥ መንገድ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቱ የዜጎችን ችግር የሚያባብስና ሕገ ወጥ ስምምነት መሆኑን በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ተወካዮች ጋር ያደረገው ስምምነት በእጅጉ የሚያስደነግጥና ወደፊት በአካባቢው የሚፈጠረውን ችግር ለመገመት የሚከብድ እንደሚያደርገው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ ገልጸዋል። መብራቱ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ከሆነ፣ የስምምነት ሰነዱ ለታጣቂው ኃይል በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ስልጣን ለማጋራት እና የታጣቂው ኃይል አባላትን በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ለማካተት የተፈረመ መሆኑን ጠቁመዋል።
“በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት የኃላፊነት ቦታን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ ነገር ግን የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ ጫካ ገብቶ ሕዝብ ከጨፈጨፈ ኃይል ጋር ስልጣን ለማጋራት መስማማት እጅግ በጣም አስገራሚ ታሪካዊ ስህተት ነው” ብለውታል መብራቱ። ፓርቲው አካባቢውን በንቃት እንደሚከታተል የጠቆሙት መብራቱ ስምምነቱ የክልሉን ህዝብ ፍላጎት ያማከለ እንዳልሆነ እና የግለሰብ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል።
ማንኛውም ቡድን የኃይል ትግል አቁሞ ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሱ በራሱ ችግር እንደሌለው የገለጹት መብራቱ፣ በታጣቂው ኃይል የተጎዳውን ማሕበረሰብ ሥነ ልቦና ባልጠበቀና ፍላጎቱን ባላማካለ ሁኔታ የተደረገ ስምምነት የዜጎችን መብት የሚገድብና ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ አክለዋል ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። በታጣቂ ኃይሉ ቤት ንብረታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ዜጎች ሳይረጋጉና ተገቢውን ካሳ ሳያገኙ ከችግሩ ፈጣሪ ጋር መስማማት ተገቢ አለመሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህ ቀደም የታዩት ተሞክሮዎች ውጤታማ አለመሆናቸውን የሚስታውሱት መብራቱ፣ የተወሰኑ ኃይሎችን ሰብስቦ ተሃድሶ ሰጥቻለሁ ማለቱ ፍሬ የሚያስገኝ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሌ ሐሰን ከታጣቂ ኃይሉ ጋር ስምምነት ሲያደርጉ በታጣቂ ኃይሉ እና በመከላከያ መካከል በካማሽና በጉባ ወረዳዎች የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የገለጹት መብራቱ፣ በአንድ በኩል ስምምነት በሌላ በኩል የኃይል ትግል ለውጥ አያመጣም ብለዋል።
“ነፍጥ ይዞ፣ የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ ጫካ ገብቶ ንጹሐን ዜጎችን ለሚገድል ታጣቂ ኃይል፣ በአቋራጭ ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ ስልጣን የሚሰጥ ከሆነ ምርጫ ማድረጉ ምንም ትርጉም የለውም” ሲሉ መብራቱ የጉዳዩን ሕገ ወጥነት ገልጸውታል።
አዲስ ማለዳ የታጣቂው ኃይል ሰለባ ሆነው የተፈናቀሉ ዜጎችን አነጋግራ ስምምነቱ ችግራቸውን ከማባባስ በዘለለ ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸዋል። ለዚህም እንደ ማሳያት የሚያነሱት ከዚህ በፊት የታጣቂው ኃይል አባላት ተስማምተናል ብለው የተሃድሶ ስልጠና ወሰዱ ተብሎ በነበረበት ወቅት የቦታውን መውጫ መግቢያ አጥንተው መልሰው ከድተው ጥቃት እንዳደረሱባቸው አስታውሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በተስማሙበት የስምምነት ሰነድ ውስጥ ከታጣቂ ሃይል አባላት መካከል አቅምና የትምህርት ደረጃቸውን በማየት በክልል ደረጃ 2 ፣ በዞን ደረጃ 3 እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ 4 የኃላፊነት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የከተማ የቤት መስሪያ ቦታ፣ የገጠር የእርሻ መሬት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሴቶችን በማካተት በተለያዩ ማህበራት እንዲደራጁ ማስቻል፣ በተማሩበት የሙያ መስክ እንዲመደቡ ማድረግ፣ ከአሁን በፊት ልምድ ያላቸውን ሰዎች በክልሉ ውስጥ ባሉ የጸጥታ መዋቅሮች መመደብ እና የብድር አገልግሎት መስጠትን የመሳሰሉ ሀሳቦች ይገኙበታል።
ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013



