የስኳር ኮርፖሬሽንን ወደ ግል ለማዞር አማካሪ ሊቀጠር ነው ተባለ

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ለስኳር ኮርፖሬሽን ፕራይቬታይዜሽን አማካሪ ሊቀጥር መዘጋጀቱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። በፕራይቬታይዜሽን ዕቅድ መሠረት በሽያጭ ወደ ግል ከሚዘዋወሩት መካከል አንዱ ለሆነው የስኳር ፕሮጀክት አማካሪ ለመቅጠር ሁለት ካምፓኒዎች እየተመገሙ መሆኑን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ወንዳፍራሽ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አማካሪ ለመቅጠር የወጣውን የጨረታ ሰነድ ከገዙት ስድስት ድርጅቶች መካከል ሁለት ድርጅቶች ማለትም Price water house Cooper Limited (PwC) እና Ernst &Young Global Limited Certified Accountants የተባሉ የውጭ ድርጅች ብቻ የፋይናንሻል እና ቴክኒካል ዶክመንቶችን አቅርበዋል።

እነዚህ ድርጅቶች ከኹለት ሳምንት በፊት በተከፈተው ጨረታ ያቀረቡት ቴክኒካል ዶክመንት በኤጀንሲው እየተገመገመ መሆኑን ወንዳፍራሽ ጠቁመዋል። አሁን ኤጀንሲው የሚገመግመው ቴክኒካል ዶክመንት እንደተጠናቀቀ የሚቀጠረውን አማካሪ ማወቅ ይቻላል ብለዋል።
ቀሪዎቹ አራቱን ሰነድ የገዙት ድርጅቶች Booker Tate Limited, United Kingdom Deloitte Consulting Limited, Grant Thornton International እና PGBI project (Pty) Ltd ሲሆኑ ጨረታው ሲከፈት ፕሮፖዛላቸውን እንዳላቀረቡ ወንድአፍራሽ ገልፀዋል።

‘ፕራይቬታይዜሽን’ ወይንም የመንግሥት ድርጅቶችን ለግል ይዞታነት የማዞር ጉዳይ በርካታ ምሁራንን ሲያነጋግር የቆየ ጉዳይ ቢሆንም በመጨረሻም መንግስት ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስፈልጉ ሂደቶችን በማሟላት ላይ ይገኛል። ከስኳር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ወደ ግል የሚዞሩ በመንግስት ተይዘው ከነበሩት ተቋማት መካከል አየር መንገድ፣ ባንክ፣ ቴሌኮም እና የባቡር አገልግሎት ይገኙበታል። ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ፈሰስ የተደረገው ሀብት የታሰበውን ውጤት ሳያመጣ መቅረቱ የሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ዕዳ ወለዱን ሳይጨምር 149 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህንንም ተከትሎ የስኳር ፕሮጀክቶች የሚያስተዳድረው ስኳር ኮርፖሬሽን የመንግሥት እቅድ ወደ ሆነው ፕራይቬታይዜሽን ተካቷል።

ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 79.9 ቢሊዮን ብር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ የብድር ዕዳ እንዳለበት ይጠቀሳል። በ42 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው የስኳር ኮርፖሬሽን፣ በ2003 ዓ.ም. እንደሚኖር ከሚጠበቀው የ2.2 ሚሊዮን ቶን የስኳር ምርት በ2007 ዓ.ም. ወደ 3.7 ሚሊዮን ቶን፣ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም. ወደ አምስት ሚሊዮን ቶን የሚያሻቅብ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይፋ አድርጎ ነበር። የስኳር ኮርፖሬሽን ለስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከአገር ውስጥ ባንኮች 95.7 ቢሊዮን ብር የተበደረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የተለቀቀለት 90.2 ቢሊዮን ብር ነው። ኮርፖሬሽኑ ከአገር ውስጥ ካገኘው ብድር ውስጥ በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ ታኅሳስ 2019 መጨረሻ ድረስ 8.59 ቢሊዮን ብር ተመላሽ በማድረጉ፣ ቀሪ 81.64 ቢሊዮን ብር ዕዳ አለበት።

ኮርፖሬሽኑ ከአገር ውስጥ ባንኮች በተጨማሪ ለፋብሪካ ግንባታ፣ ለማሽነሪ ግዥና ለጠብታ መስኖ ማስፋፊያ ከቻይና ባንኮችና ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ያገኘ ሲሆን 2.24 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ እንደተለቀቀለት የሚታወስ ነው። ከዚህ የውጭ ብድር ውስጥ በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ ታኅሳስ 2019 መጨረሻ ድረስ 137,562,190 ዶላሩን ተመላሽ በማድረጉ፣ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ቀሪ ዕዳ አለበት።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here