በክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች የቡና ምርትና አቅርቦት አለመቀነሱ ተገለጸ

0
718

በኢትዮጵያ የቡና ምርት የሚያቀርቡ ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች የማምረት አቅማቸው አሁንም በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳህለሥላሴ ገ/መድህን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከምታገኝባቸው መካከል በኦሮሚያ ክልል እንደ ወለጋ ያሉ አካባቢዎች የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ይታወቃል።
ቢሆንም ግን ይህንን ስጋት ተከትሎ በክልሉ የቡና ምርት መቀነስ አለመኖሩን ነው ሳህለሥላሴ የተናገሩት።
በባለፉት 4 ወራት ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና መገኛ በሆኑ ኹሉም ክልሎች በኩል ቡና መገኘቱንና ለውጭ ገበያ መቅረቡን ሳህለስላሴ ጠቁመዋል።
እንደ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር 2013 ወደ ውጭ አገራት ከላከችው የቡና ምርቷ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር አንጻር ሲታይ አነስተኛ መጠን ያለው መሆኑ ነው የተገለጸው።
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ የሆነውም በዚህ አመት የአዲስ ቡና ምርት ወደ ገበያ መግባቱ እና የነበረውን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የመጣ መሆኑን ሳህለሥላሴ ጠቁመዋል።
አምና ወደ ውጭ ከወጣው ቡና አንጻር መጠኑ በጥቂቱ የቀነሰ ቢሆንም፣ ከዋጋ አንጻር ሲታይ ግን ከፍተኛ ጭማሪ የታየበትና አምና በአንድ ቶን ይገኝ የነበረው 3700 ዶላር ወደ 4000 ዶላር ከፍ ማድረግ የተቻለበት ነው ተብሏል። ጭማሪውም ወደ 10 በመቶ መሆኑም ታውቋል።
ይኸውም በግንቦት ወር ብቻ ወደ ውጭ አገር ከተላከ 32 ሺሕ 669 ቶን ቡና 130 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
አዲስ የቡና ምርት ማለት በአዲስ በጀት ዓመት የተሰበሰበው ቡና ማለት ሲሆን፣ አዲስ የበጀት ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ያለው የቡና ምርት እንደሆነ ሳህለሥላሴ ተናግረዋል።
አሁን አዲሱን ቡና መጠቀም ከተጀመረ ጀምሮ በየወሩ እድገት እያታየ በመሆኑ በቀጣይ ኹለት ወራት ውስጥ ደግሞ የተሻለ የውጭ ንግድ ይኖራል ብለዋል።
ቡና በተለይም ከጥር ወር ጀምሮ ወደ ገበያ ከተቀላቀለው አዲሱ የቡና ምርት ጋር ተያይዞ ለባለፉት አራት ተከታታይ ወራት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ እያሻቀበና ያለማቋረጥ ጭማሪዎች እየታዩበት ይገኛል።
በመጋቢት ወር ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ካቀረበችው 27 ሺሕ 200 ቶን የቡና ምርት ላይ በአንድ ወር ብቻ ከ107 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝታ እንደነበር ይታወሳል። በሚያዝያ ወር ደግሞ 28.8ሺሕ ቶን ቡና ተልኮ 114 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይኸው የገቢ ግኝት በግንቦት ወር 130 ሚሊዮን ዶላር ሊገኝ ችሏል።
በአጠቃላይ በነዚህ 4 ወራት ለዓለም ገበያ በቀረበው ቡና የነበረው አፈጻጸም ከ100 ፐርሰንት በላይ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ቡናዎች ጥራታቸው እየተጠበቀ ወደ ገበያ መግባታቸውን እና በዋጋ ደረጃ ዓለም አቀፉን ገበያ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ መቀላቀል መጀመራቸውን የሚያሳይ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እየተከናወነ የሚገኘው የምርጥ ቡና ውድድርም ቡና በጥራት እንዲመረት የራሱን አስተዋፆ አደርጓል ተብሏል።
ከግብርና ኤክስፖርት ምርቶች ቡና የመሪነት ሚናውን እንደያዘ የሚገኝ ሲሆን፣ እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬም የአገሪቷን ፈጣን ልማት ለማምጣት የተያዘውን ጥረት የሚደግፍ፣ አርሶ አደሩም ከሚገኘው ገቢ የተሻለ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚሄድ ማሳያ ነው ሲሉ ሳህለሥላሴ ጠቁመዋል።
ለተገኘው ገቢ የአርሶ አደሩና ላኪው እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው በማለት ሳህለሥላሴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የገበያ አማራጭ መስፋታቸውና አርሶ አደሩ በቀጥታ ወደ ውጭ የሚልካቸው የቡና ምርቶች ከቡና የሚገኘውን ገቢ እንዲያድግ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ መጠን ያለዉ የቡና ምርት ከሚያቀርቡ አገሮች አንዷ ብትሆንም፣ የቡና አምራቾች የምርቱን ያህል በገበያው ተጠቃሚ አለመሆናቸው ይታወቃል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግብይት ሰንሠለት ጠብቆ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበዉ ቡና አምራቹ አርሶ አደር 35 በመቶ ብቻ ተጠቃሚ ነዉ። ቀሪዉን 65 በመቶ በግብይት ሰንሠለት ላይ ያሉ ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጠቃላይ የቡና ምርት 40 ከመቶ ገደማ የመሸፈኗን ያህል በዚሁ መጠን ምርቱን ወደ ዓለም ገበያ ማቅረብ ብትችል እጅጉን ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ይታወቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here