ብዙ የተደከመበትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሊከናወን ከ48 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።የምርጫ ቅስቀሳ ተጠናቆ ፓርቲዎች ምንም አይነት የምርጫ እንቅስቃሴ ከማድረግ የሚቆጠቡበት የጥሞና ጊዜ ላይ እንገኛለን።ቅስቀሳው ከመጠናቀቁ በፊት በተለይ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ቀናት ቅስቀሳው ተጠናክሮ መንገድ ተዘጋግቶ ጭምር ነበር። በየአደባባዩና በየአውራ ጎዳናዎች ላይ የነበረው የቅስቀሳ ሂደት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሁኖ ነበር። በሥራ ሰዓት መንገድ ተዘግቶ ቅስቀሳ መደረጉ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው ላይ ለመነጋገር አሁን ጊዜው ባይሆንም፣ የብዙዎችን ትዕግስት ያስጨረሰና ያማረረ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል። በ5 ዓመት አንዴ የሚሆን ቢሆንም ሕግና መመሪያ ተጥሶ መሆን ስለሌለበት ለቀጣዩ ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
የምርጫው ቅስቀሳ በቆመበት በዚህ የጥሞና ጊዜ ያልቀረው ነገር ቢኖር በፖስተርና ባነሮች አማካይነት መቀስቀሱ ነው።በየመንገዱ ደሴቶች ላይ በማስታወቂያ መልክ ከተለጠፉት በተጨማሪ፣ በየስልክ እንጨቱና አጥር ላይ በእሽቅድምድም ሲለጠፉ የነበሩት የመቀስቀሻ ምስሎች እልባት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አጥሩ ላይ ማስታወቂያዎቹ ተለጥፈው ያገኘ ግለሰብ ያለፍቃዱ በመደረጋቸው ማስነሳት እየቻለ እራሱ ቢያነሳቸው በወንጀል ሊያስጠይቀው እንደሚችል በመገመት አይነካቸውም። በጥሞናው ጊዜ እንዳሉ ከመቆየታቸው ባሻገር እንደ ኢህአዴግ የንብ ማስታወቂያ ለአመታት ተለጥፈው አለመቅረታቸውን እርግጠኛ ሆኖ መናገርም አይቻልም።በጥሞና ጊዜው ፖለቲከኞች መቀስቀስ የማይችሉት ድምጻቸውን ተጠቅመው በመገናኛ ብዙኃን ቢሆንም፣ ያስለጠፉትን ግን ማንሳት አይጠበቅባቸውም።
በሌላ በኩል፣ የቲሸርት መቀስቀሻ መንገድም በተመሳሳይ ውሳኔ ያገኘ አይመስልም። በችግር ይሁን በፍላጎት ባይታወቅም በጥሞናው ጊዜ አንዳንዶች ለብሰው ሲዘዋወሩ መታየታቸው አልቀረም። ምርጫ ቦርድ ማንኛውንም አይነት ምርጫ ተኮር ቅስቀሳም ሆነ እንቅስቃሴ ቢከለክልም፣ የትኛው ተግባር የተፈቀደ እንደሆነ በዝርዝር ስላላብራራ ለአስፈጻሚዎቹ ምቹ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ተመራጮች በቀጥታ ቅስቀሳ ማድረግ መከልከላቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ሚዲያዎች ስለምርጫው አጠቃላይ ዘገባ ከመሥራትና አስተያየት ከመጠየቅ እንዳልተከለከሉ ግልጽ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ-መጠይቅ በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ይቀርባል መባሉ የፈጠረው ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ፣ ተወዳዳሪ ዕጩን ስለማንኛውም ጉዳይ እየጠየቁ ማስተዋወቁ ተገቢ አይሆንም። ስለምርጫ ሂደቱም ሆነ ምርጫ ቦርድ ስላጋጠመው እክል፣ እንዲሁም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ የሚያስችል ቅስቀሳ ወይም የግለሰቦችን አስተያየት በዘገባ መልክ ማቅረቡ ወገንተኛ እስካልሆነ ድረስ የተከለከለ አይደለም። ይህን በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ከምርጫ ቦርድ ስላልወጣ በደፈናው ከምርጫ እንቅስቃሴ ታቀቡ ማለቱ ጭራሽ ስለምርጫ አታውሩ ብሎ መገደብን እንደማያስከትል ግልጽ ነው።
የጥሞና ጊዜው ዓላማ፣ ምርጫ ቦርድ ሕዝብ በምርጫው እንዲሳተፍ ራሱ የሚቀሰቅስበት የመሸጋገሪ ጊዜ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ተግባር በተመሳሳይ መልኩ ምርጫ እስኪጠናቀቅ በተለያዩ አገራት ተግባራዊ ይደረጋል። በምርጫው ቀንም መቀስቀሻ ቲሸርትን ለብሶም ሆነ ፖስተርን ይዞ ምርጫ ጣቢያ መጠጋትም ሆነ መለጠፍ አይቻልም።ይህ የሚደረገው ሕዝቡ እንዳይወናበድና ለአጭበርባሪዎች እንዳይጋለጥ ነው።
ከአመት በላይ ሲለፋበትና ለችግራችን እንደ አንዱ መፍትሄ ተደርጎ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው ይህ ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱን ለመስማት ብዙዎች ጓጉተዋል። ይህን ያህል ትኩረትን የሳበ ምርጫ የሚጠበቀውን ውጤት ካላመጣ እንደ 1997ቱ መማሪያ እንጂ ለውጥ ማምጫ እንደማይሆን እሙን ነው። ሰው ምረጥ ተብሎ ሊገደድ ባይችልም፣ መምረጥ የፈለገ ድምፁ እንዲከበርለት ይፈልጋል።ይህን የሚፈልግ ደግሞ የሌላውን ማክበር ይጠበቅበታል።ከምርጫው በፊት የነበረው ሂደት ከሞላ ጎደል ውጤታማ ነበር ማለት ቢቻልም፣ ምርጫውና ድህረ ምርጫውም ውጤታማ እንዲሆን የኹላችንም ጥረት እንደሚያስፈልግ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በድህረ ምርጫ ተጭበረበረ ብሎ ለመካሰስ ከመቸኮል በፊት ሂደቱ ላይ በመገኘትና በመከታተል ለአጭበርባሪዎች ዕድል ላለመስጠት መሠራት አለበት። አወናባጅና አጭበርባሪ አይኖርም ብሎ ማመን ስለማያዋጣ፣ የጸጥታው ሥራ እንደሚከናወነው የቁጥጥር ሥራውም ጎን ለጎን በቅንጅት መከናወን አለበት። በየዋህነት መተማመኑ ቀርቶ፣ አንዱ አንዱን በቁራኛ እየተከታተለ ሂደቱ መጠናቀቅ አለበት።ማጭበርበር ከተፈጸመ እያዩ ዝም ከማለትና አጠቃላይ ሂደቱ ተቀባይነት እንዲያጣ ከማድረግ ይልቅ፣ የአገርና የሕዝብ ሐብት ባክኖ እንዳይቀር የመከላከሉ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ምርጫው በሚካሄድበት ዕለት በየጣቢያው መቅረብ የተፈቀደላቸው ከለሊት ጀምሮ ተገኝተው በሩ ከመከፈቱ በፊት ኹሉ ነገር በሥርዓቱ ማደሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በፊት በነበሩት ይደረግ ነበር እንደሚባለው፣ አጭበርባሪ ፖለቲከኞች በጠዋት ቀድመው መጥተው በመመሳጠር ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ መከታተል ያስፈልጋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ሂደቱን ተደብቀው ማየት ብቻ ሳይሆን፣ በግላጭ እየተከታተሉ መሆኑን ማሳወቃቸው ክፉ ነገር እንዳይታሰብ ስለሚያደርግ አስቀድመው በሚሠሩት ሥራ የመከላከልን ተግባር ውጤታማ ማድረግ ይችላሉ። ኹሉም ሰው ሂደቱን ለሚከታተሉ ሰዎች የሚጠጣና የሚበላ በማቅረብ እገዛ ማድረግም ይጠበቅበታል። የሚመርጡ ሰዎችን ማንነት የማጣራት ተግባር በዋናነት የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ቢሆንም፣ ለየት ያለ እንቅስቃሴን ኹሉም በአትኩሮት ሊከታተል ይገባል። ምርጫው ተከናውኖ ቆጠራው ሲካሄድም ከመከታተል በተጨማሪ ውጤቱ ተልኮ በአግባቡ ለመመዝገቡ የሚከታተል አካል ከኹሉም ወገን ቢዘጋጅ መልካም ነው።
በሂደቱ ስህተትም ሆነ ችግር ቢፈጠር በቀጥታ ለሕዝብ ማሳወቁ እርምት እንዲወሰድ አያደርግም።ለሚመለከተው ምርጫ ቦርድ ወይም የጸጥታ አካላት ማሳወቁና ማስረጃውንም ሆነ ጥቆማውን ማስተላለፉ የሁላችንም ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። ለነዚህ አካላት ማቅረብ ያልቻሉ ለሚያምኑት ወገን በውስጥ መስመር በማስተላለፍ እንዲታወቅ ማድረግ እንጂ፣ ለሕዝብ ወዲያው ማሰራጨቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በትክክለኛው መስመር ተጉዞ መፍትሄ ካልተገኘለት የሆነውን ለሕዝብ ማሳወቁ ተገቢ ቢሆንም፣ ታስቦበት ሊሆን ይገባል። “ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንደሚባለው ለአጭበርባሪዎችም ሆነ ለጠላቶቻችን እድል ላለመስጠት መተባበር ያስፈልጋል።


