የላፕሴት ፕሮጀክት የጅቡቲ ወደብን ከመጠቀም አያግድም ተባለ

‹‹ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በጅቡቲ ወደብ የምታንቀሳቅሰውን 17 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ወደ 33 ሚሊዮን ቶን ታሳድጋለች››

ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው የላፕሴት ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን ከመጠቀም አያግዳትም ሲሉ የፍራይተር ኢንተርናሽናል (ፓቦሚ) ኃ.የተ.የግ.ማኅበር መሥራች የሆነው ዳንኤል ዘሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናገረ።
ጅቡቲ በዋናነት እስከዛሬ የሚደረገውን የኢትዮጵያን የንግድ እንቅስቃሴ የምትመራ ሲሆን፣ ከአቅም በላይ መጨናነቅ የሚፈጠርባት ከሆነ እንደ በርበራ እና ላሙ ያሉ ወደቦች ያግዟታል እንጂ አገልግሎቷን አያስተጓጉሉም ሲሉ ዳንኤል ተናግረዋል። ዳንኤል እንደ ምክንያት ያነሱት አንደኛ ጉዳይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማለትም ከደቡብ፣ከምስራቅ፣ ከሰሜንና ከምዕራብ የሚገቡ ዕቃዎች መጠን የሚጨምር መሆኑን ነው።

‹‹ጅቡቲ ላይ የዕቃዎች መጨናነቅ ሲኖር የእነዚህ ወደቦች መኖር አስፈላጊ ነው። እንደ አሰብ ያሉ ወደቦች ለኢትዮጵያ አማራጭ ናቸው። ወደፊት ደግሞ እነዚህ ወደቦች የየራሳቸው አንድ አገልግሎት ላይ ብቻ በመሰመራት አቅማቸውን እያሳደጉ የሚሄዱ ናቸው። እነዚህ ወደቦች ከኮንቴይነር ይልቅ ብትን እቃዎችን ማስተናገድ የሚችሉበት ብቃት አላቸው›› ሲሉ ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ የሚጠበቀው በሚመጡት 5 አመታት ውስጥ ከምናንቀሳቅሰው 17 ሚሊዮን ቶን የዕቃ መጠን ወደ 33 ሚሊዮን ቶን ወደ ማንቀሳቀስ ማሳደግ ነው። ይህ የዕቃዎች እንቅስቃሴ የሚጨምር ከሆነ ሁሉንም ወደቦች ለመጠጠቀም የሚያስችል አቅም ይኖራል ብለዋል።

የላፕሴት ፕሮጀክት በአፍሪካ ንግድ መዋቅር ውስጥ በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ለሆኑ አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት አገር በመሆኗ የተለያዩ ወደቦችን መጠቀም ግድ መሆኑን ነው ዳንኤል ያነሱት።
ይህ የላፕሴት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የገቢና የውጪ እቃዎች ንግድ በአግባቡ ለማስተናገድ ያግዛል። እንደ ዳንኤል ገለጻ ከሆነ፣ አገልግሎቱ እንደሚታወቀው ተወዳዳሪ የዋጋ እና የጥራት ደረጃ ያስፈልገዋል። በአንድ ወደብ ብቻ ተማምኖ መቀመጥ ለአገልግሎት የሚከፈልን ክፍያ ለመቆጣጠር ያስቸግራል ብለዋል።

በዓለም የሺፒንግ አሠራርን ስንመለከት ስዊዘርላንድ የራሷ ወደብ የላትም ነገር ግን አውሮፓ ላይ ከሜድትራንያን ወደብ ጀምሮ እስከ ሰሜን አውሮፓ ድረስ ከ10 በላይ ወደቦች ትጠቀማለች። ምክንያቱም ሁሉም ወደብ የየራሱ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ነው። ጅቡቲ ኹልጊዜም የመጀመሪያው አማራጭ አገር እንደመሆኗ መጠን እና ከኢትዮጵያ ባህሎችና ሕዝቦች ጋር አብራ የምትሄድ፣ እንዲሁም ትልቅ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላት አገር ስለሆነች ኢትዮጵያ ወደቧን መጠቀም አታቆምም ብለዋል። ወደብ የአገር ደም ስር ነው የሚሉት ዳንኤል፣ የወደብ እንቅስቃሴዎች በተፈለገው ደረጃ እንዲያድጉ ማደረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዚህም የወደቦች መስፋፋት ለኢትዮጵያ ፈጣን የሆነ የኢንዱስትሪ ፍሰት ያሰፋል።

የሎጂስቲክ ዘርፍ የግል ወይንም የመንግሥት ተቋም በማለት የሚለያይ አይደለም የሚሉት ዳንኤል፣ እንደ ግልም ሆነ እንደ መንግሥት ተቋም ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በተፈለገው ፍጥነት ማጓጓዝ ግድ ነው ብለዋል። በሌሎች ዓለም አገራት የግል ድርጅቶች በራሳቸው ከወደቦቹ ባለቤቶች ጋር አደረጃጀት መፍጠር ይቻላሉ። በእኛ አገር ግን በመንግሥት በኩል ብቻ በመሆኑ ፖሊሲዎችን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን ለማስተሳሰር ያለመው የላፕሴት ፕሮጀክት በፍጥነት መንገድ፣ ባቡርና ሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶች አማካይነት አገራቱን የሚስተሳስር ነው።

ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላለው ለአህጉሪቱ ኢኖሚያዊ ውህደት መፋጠን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ተብሎለታል። የላፕሴት ፕሮጀክት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለማስፋት የሚረዳ ነው። የላፕሴት ፕሮጀክት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ነበር በሦስቱ አገራት መሪዎች የጋራ ሥምምነት ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ የተላለፈው።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here