ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዲዘጋ መወሰኑ ቅሬታ አስነሳ

ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እውቅና ሳያገኝ አዳዲስ ተማሪዎችን በመቀበል አስተምሯል እና ድንበር ተሻጋሪ ትምህርቶችን ያለፍቃድ ሰጥቷል በማለት እንዲዘጋ የተወሰነው ያለ አግባብ ነው ሲሉ የኮሌጁ መስራች እና ፕሬዝዳንት አቤቱ መላኩ ቅሬታቸውን ገለጹ።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ታረቀኝ ገረሱ በበኩላቸው፣ ማንኛውም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በከፍተኛ ትምህርት በመረጠው የትምህርት መስክ ደረጃና መርሃ-ግብር ለማስተማር ከኤጀንሲው የእውቅና ፈቃድ ይሰጠዋል። ይህ የተሰጠው ወይም ተሰጥቶት የነበረው እውቅና ፈቃድ ሊታደስለት እንደሚገባ እየታወቀ፣ ዌስተርን ኮሌጅ እስከአሁን ድረስ ዕድሳት ባለማድረጉ ለመዝጋት ተገደናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ዌስተርን ኮሌጅ ከሕግ ውጪ በመስራቱ የእርምት እርምጃ ተላለፈበት በማለት በተለያየ ሚዲያ ኤጀንሲው ያሰራጨው መረጃ፣ እንዲሁም ተቋማችንን መዝጋቱ አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ አቤቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አቤቱ አክለውም ኤጀንሲው ይህንን የእርምት እርምጃ የወሰደብን የዕድሳት ፈቃድ ጠይቀን ለጥያቄው ምላሽ በሰጡ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው ብለዋል። ዌስተርን ኮሌጅ ሰኔ 16/2013 ከኤጀንሲው በደረሳቸው መረጃ መሰረት የዕውቅና ፍቃድ ዕድሳት ለመውሰድ በቅድሚያ 500ሺሕ ብር የባንክ ዋስትና ማስያዝና የተቋሙን የተማሪዎች መረጃ በኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህር መረጃ ሥነስርዓት አስተዳደር ማስገባት እንዳለባቸው ተገልፆላቸው ነበር።

ይሁን እንጂ የፈቃድ ዕድሳት ለማግኘት የተጠየቅነውን ሥራ በመሥራት ላይ እያለን ኤጀንሲው መጥቶ ተቋሙን ዘግቶታል ሲሉ አቤቱ ገልጸዋል። አያይዘውም ‹‹ተቋማችን ከ10 ዓመት በላይ ከማስቆጠሩም ባለፈ፣ በርካታ ዜጎችን ማፍራት የቻለ መሆኑ እየታወቀ በዚህ ፍጥነት ይህን አይነት እርምጃ መውሰድ ትውልድ ላይ እንደመፍረድ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ አሜሪካ አገር ከሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተለያዩ ፕሮግራሞች ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል።

በቅድመ-ምረቃ ደረጃ እና በመደበኛ መርሃ-ግብር በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የትምህርት መስክ እንዲሁም በድህረ-ምረቃ ደረጃ በድንበር ተሸጋሪ መርሃ-ግብር አሜሪካ አገር ከሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የትምህርት መስክ ለማስተማር እስከ 2012 ድረስ ታድሶለት የነበረውን የዕውቅና ፈቃድ በመጠቀም የትምህርት አገልግሎት መስጠቱን ኤጀንሲው አስታውሷል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ 1152/2011 አንቀጽ ቁጥር 79 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት 500 ሺሕ ብር በዝግ የባንክ አካውንት በማስቀመጥ ወይም ደግሞ ተመጣጣኝ የንብረት ዋስትና በባንክ በማስያዝና በከፍተኛ ትምህርት የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት የተቋሙን መረጃ በማስገባት ማሳደስ ሲኖርበት ባለማሳደሱ ይህንን እርምጃ ወስደናል ሲሉ ታረቀኝ ተናግረዋል።

ታረቀኝ አክለውም፣ በቅድመ-ምረቃ በድንበር ተሻጋሪ መርሃ-ግብር አሜሪካ አገር ከሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የትምህርት መስክ የዕውቅና ፈቃድ ሳይኖረው ተማሪዎችን መዝግቦ እንደሚያስተምር በመታወቁ ጭምር ነው እርምጃው የተወሰደው ብለዋል። ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥነ-ስርዓት መመሪያ መሰረት የዕውቅና ፈቃድ ሳያሳድስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲያስተምር ቆይቷል። ስለሆነም እስከ ነሐሴ 2012 ድረስ የመዘገባቸውን ተማሪዎች ዕውቅና ወዳላቸው ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚያዛወርና ከመስከረም 2013 ጀምሮ የመዘገባቸውን ተማሪዎች እንደሚያሰናብት ታረቀኝ ገልጸዋል። ታረቀኝ አክለውም እስከ 2012 ድረስ የመዘገባቸው ተማሪዎች ዕውቅና ወዳላቸው ሌሎች ተቋማት የሚዘዋወሩት በራሳቸው ፍላጎት ሲሆን፣ ኤጀንሲው በሚያውቃቸው ተቋማት ገብተው እንዲማሩ ይደረጋል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here