በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ ፈታኝ ሆኗል ተባለ

በተለያዩ አካባቢዎች የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነበት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ። በኢትዮጵያ የወንጀል ምርመራ ሥርዓት የዐይን ምስክር ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ችግሩን አሳሳቢ እያደረገው እንደሚገኝ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተለያዩ አከባቢዎች ላይ ስለተፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎች በቂ የምስክርነት ቃል የማይሰጥ ከሆነ ወንጀለኞችን ማስቀጣት አዳጋች እንደሚሆን አስረድተዋል። ባለፉት ጊዜያት በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል እና ሌሎች ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ጉዳቶች የደረሱ ሲሆን፣ በወንጀል ምርመራ ሂደቱ ማሕበረሰቡ በቂ የሆነ የምስክርነት ቃሉን በመስጠቱ ምክንያት ዘጠና በመቶ የሚሆኑት የወንጀል ድርጊት ፈጻሚ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ ተደርገው ነበር ብለዋል።

አሁን አሁን ግን በቡድን የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከጀርባቸው ጠንካራ መረቦች ያላቸው በመሆኑ ወንጀለኞችን በቀላሉ ለመቆጣጠር እና በሕግ ለመጠየቅ እንዳይቻል ማድረጉንም ነግረውናል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሁን ባለው አቋም የትኛውም ቦታ ላይ ለተፈጸመ ወንጀል ስለ ወንጀሉ አፈጻጸም በቂ ማስረጃ ካገኘ ተገቢውን ፍርድ ለማሰጠት ብቁ ነው ብለውናል። ይሁን እንጂ፣ የሕበረተሰቡ ተባባሪነት እንደሚፈለገው ካልሆነ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ አዳጋች ያደርገዋል ነው ያሉት አወል። አያይዘውም የሕበረተሰቡ ተሳትፎ የወንጀል ድረጊት የፈጸሙ ግለሰቦች በሕግ ለሚኖራቻው ተጠያቂነት የጎላ ሚና እንደሚኖረው አስምረውበታል።

እየተፈጸመ ካለው ወንጀል አንጻር ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ አሁን ላይ እንደ አጠቃላይ ወንጀል ፈጽመው ከሕግ ያመለጡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ከሕግ ተጠያቂነት የሚያመልጥ አንድም ስለማይኖር የጊዜ ጉዳይ ሆኖ ተጠያቂ መሆናቸው የማይቀርበት ቀን ይመጣል ብለዋል። በተለያዩ አከባቢዎች ሰዎችን የገደሉ፣ ያፈናቀሉ እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ዜጎች ተገቢውን የሕግ ቅጣት ማግኘታቸው አይቀርም ሲሉ አመልክተዋል። በዚህም ጥፋተኞች ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እየሠራ እንደሆነ ነግረውናል።

ኃላፊው ባለፉት ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ውስጥ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ በማድረግ እና በሕበረተሰቡ ጥቆማ መነሻነት በስድስት ዞኖች ውስጥ ከ3,300 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን አስታውሰዋል። የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ሰዎችን በመግደልና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተሳተፉ ተከሳሾች ላይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአንድ አስከ 20 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት መጣሉንም ገልጸውልናል።
አያይዘውም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ ደንገዝ ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የንጹኃን ሕይወት ማለፉ፣ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እና ንብረታቸው መውደሙን አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም በወንበራ እና ቡለን አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ተሳትፈዋል በተባሉ አምስት ሽፍታዎች ላይም እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። በተጨማሪም የጸጥታ ኃይሉ በቅርቡ 20 ተጠርጣሪዎችን ከሦስት የጦር መሳሪያ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውሰው፣ በዞኑ እስካሁን በቁጥር የበዙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ መቅረባቸውን አንስተዋል። ሕብረተሰቡ በአንድነት አቋም ይዞ ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሆን ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት አንደሚጠበቅበት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here