በአዲስ አበባ ከተማ 102 ሺሕ ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ራሳቸውን መመገብ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዲስ ባስጠናው ጥናት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ከሚኖሩ ዜጎች ውስጥ 102 ሺሕ ያህሉ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ራሳቸውን መመገብ አለመቻላቸውን ማረጋገጡን የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና ማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አበባ እሸቴ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እንዳሉት ከሆነ፣ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ በአንድ ጊዜ የሚሸፈን እንዳልሆነ አሳውቀዋል። ከተማ አስተዳደሩ ዜጎችን በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑንም አበባ ጠቁመዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከተባባሪ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በቀን አንድ ጊዜ ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን ለመመገብ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አበባ ገልጸዋል። የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2014 ችግሩን ለማቃለል በትኩረት እንደሚሠራ የጠቆሙት አበባ፣ አዳዲስ አሠራሮችን ቢሯቸው እንደሚከተል ተናግረዋል።
በቀን አንድ ጊዜ እራሳቸውን መመገብ ከማይችሉት 102 ሺሕ ዜጎች መካካል፣ መንቀሳቀስና ምንም አይነት ሥራ መሥራት የማይችሉና ሥራ የመሥራት አቅም እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት ያልቻሉ ይገኙበታል። ቢሮው ችግሩን ለማቃለል ከነዚህ ዜጎች መካከል ሥራ መሥራት ለሚችሉ በ2014 የሥራ እድል ለመፍጠር እንሚሠራ አበባ አመላክተዋል። ለዚህም በአዲስ አበባ የሚገኙ የምገባ ማዕከላትን ከምገባ ማዕከልነት ባለፈ እንደ ማሰልጠኛ ተቋም ለመጠቀም ቢሮው እየሠራ መሆኑ ተመላክቷል። የምገባ ማዕከላት ከዕለታዊ ምገባ በተጨማሪ የማሰልጠኛ ተቋም ሆነው ማገልገል ከቻሉ፣ መሥራት የሚችሉ ዜጎችን ሥልጠና በመስጠት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው እራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል ተብሏል።
መሥራት የሚችሉት ዜጎች መሥራት እንዲችሉ በማድረግ፣ እራሳቸውን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን ቁጥር በሂደት መቀነስ እንደሚቻል አበባ ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ ይህን ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ትብብርና እገዛ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በቅርቡ የተመረቀውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከልን ጨምሮ አምስት የምገባ ማዕከላት ይገኛሉ። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገነባው 5ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ሥራ ጀምሯል። የምገባ ማዕከላቱ አቅመ ደካሞችን፣እናቶች እና አረጋውያንን ከመመገብ ባሻገር፣ መሥራት ለሚችሉ ወገኖች የሥራ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸው ተገልጿል። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሥራውን በይፋ የጀመረው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካይነት የተገነባ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድህን አክሲዮን ማኅበር የአምስት ሚሊዮን ብር፣ ሮሃ ሜዲካል ካምፓስ ሔልዝ ፋውንዴሽን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል ተብሏል። የምገባ ማዕከላት ድረስ ሄደው መመገብ የማይችሉ ዜጎች በከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል በተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣች በየቤታቸው ምግብ የማድረስ ሥራ እንደሚሠራ ተመላክቷል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013


