ምክር ቤቱ የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ

0
381

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ አራት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ አመት የስራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶችንና አዋጆችን አጽድቋል።

የብድር ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር ያደረገቻቸው የተለያየ መጠን ያላቸው ሲሆኑ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ምጣኔ ሃብት መሰረት የመጣል ፕሮጀክት፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝና ላልተማከለ የኤሌክትሪክና መብራት አቅርቦት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ መሆናቸውም ታውቋል።

በተጨማሪም ለፍትሃዊ መሰረታዊ አገልግሎት ሁሉን አቀፍ እድገት ተጠቃሚነት መርሃ ግብር የሚውሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ የተገኙት ብድሮች ከወለድ ነጻ መሆናቸውንና ፕሮጀክቶቹን በመደገፍ ያላቸውን አስተዋጾ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።

የብድር ስምምነቶቹ ከኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውና የመክፈያ ጊዜውን በሚመለከት ከምክር ቤት አባላት ለተነሳውም ጥያቄ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ  የሚጣጣሙና ጫናቸው ያልበዛባቸው መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ላይ ተወያይቶ የቀረቡለትን አራት የብድር ስምምነቶች ረቂቅ አዋጆች አጽድቋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቻርተርና የተባበሩት መንግስታት የመንገድ ትራፊክ ስምምነት ረቂቅ አዋጅም አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ አጽድቋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት በህገ-መንግስቱ የተሰጡትን ሃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ከ20 አመታት በላይ ያስቆጠረ ክፍተቶች የሚስተዋሉበተ በመሆኑ ማሻሻያ ማድረግ እንዳስፈለገ ተገልጿል።

በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቡ ብርኪ፤ የተሻሻለው አዋጅ አሁን ያለውን የአገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የፌደሬሽን ምክር ቤት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እንዲከበር ሌሎች የተሰጡትን ተግባራት በብቃት ለማከናወን ያግዘዋል በማለት ምክር ቤቱ ማፅደቁንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን ለማቋቋም የወጣውን የማሻሻያ አዋጅም ምክር ቤቱ አፅድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም 38 አዋጆችን ማጽደቁንና 11 ውሳኔዎችን መወሰኑ ታውቋል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here