25 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት እና አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

0
1214

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 25 ሺህ ሃሰተኛ ብር እና አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል ባለ 200 የብር ኖቱን በባለ ቀለም ማተሚያ ማሽን ስታባዛ የነበረች ግለሰብ ትገኝበታለች ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ/ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ግራር ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ ወደ ሱቅ በመሄድ የሞባይል ካርድ ለመግዛት ባለ 200 የብር ኖት እንደሰጠ እና ባለሱቆቹም የተቀበሉትን ብር ተጠራጥረው ወዲያውኑ ለፖሊስ በማሳወቃቸው ፖሊስ በፍጥነት ደርሶ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎታል፡፡

ግለሰቡ ለባለ ሱቁ የሰጠው ገንዘብ ሃሰተኛ ስለመሆኑ መረጋገጡን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ በወቅቱም ኪሱ ሲፈተሽ ተጨማሪ 3ሺህ 800 ሃሰተኛ ብር መገኘቱን ገልጿል፡፡ የሃሰተኛ ገንዘቡን ምንጭ ለማወቅ ፖሊስ ባደረገው እንቅስቃሴ ተጨማሪ 3 ተጠርጣሪዎች መያዙን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በአንደኛው ግለሰብ ኪስ 1ሺህ 200 መቶ፣ በሌላኛው ግለሰብ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 20ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት ተገኝቷል፡፡ ሶስተኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ አንዱን ባለ 200 ሃሰተኛ የብር ኖት 15 ብር እየተከፈላት በባለ ቀለም ማተሚያ ማሽን ለሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ስታባዛ የነበረች መሆኗን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቋል፡፡

በአጠቃላይ 4 ተጠርጣሪዎች እና 25 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት እንዲሁም ሲገለገሉባቸው የነበሩ ፕሪንተር ማሽን እና ኮምፒውተር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here