በአዲስ አበባ ግብር ከፋዮች የሚገጥማቸውን ሰልፍ ለማስቀረት የሚረዳ በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ አሠራር ነገ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
አዲሱ አሠራር ግብር ከፋዮች የተተመነላቸው ግብር መጠን እንዲሁም የሚከፍሉበትን ባንክ በSMS አጭር የጽሑፍ መልእክት እንዲደርሳቸው የሚያደርግ ሲሆን የተገልጋዮችን ጊዜ እና ጉልበት ይቆጥባል፤ የኮቪድ-19 ስርጭትንም ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል።
አዲሱ አሠራር ሥራውን በግማሽ የሚያቃልል መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በ2013 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደውን 42 ቢሊየን 479 ሚሊየን ብር ሙሉ በሙሉ ገቢ ማሰብሰቡንም ኃላፊው ገልፀዋል።
ቢሮው በእቅድ የያዘውን ገቢ ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ የቻለው የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወኑ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራቱ እንደሆነ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ቢሮው ከነገ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ጀምሮ የ2014 የግብር ማሳወቂያ እና ማክፈያ ጊዜንም ለማስጀመር የሚያስችል ሙሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ይፋ አድርጓል።
በ2014 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ካፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ሲሆን የደረጃ ‘ለ’ ግብር ከፋዮች ግብር መክፊያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሆን ተገልጿል።
የደረጃ ‘ሀ’ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የግብር መክፊያ ጊዜ ደግሞ ከሐምሌ 1 ጥቅምት 30 ቀን 2014 እንደሚሆን ተገልጿል።
ቢሮው በ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያ አራት ወራት ውስጥም 20 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ነው ተብሏል።
ከነገ ጀምሮ በከተማዋ የሚገኙ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ (298 ሺህ 964 ነጋዴዎችን) የሚገጥማቸውን ሰልፍ ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ አሠራር ይፋ እንደሚደረግ ነው መገለፁን ከኢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ ከ418 ሺህ በላይ ግብር ካፋዮች ይገኛሉ።



