መቄዶንያ ቃል ከተገባለት 100 ሚሊዮን ብር 10 በመቶውን ብቻ ማግኘቱን ገለጸ

0
953

የመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከተለያዩ ተቋማት ቃል ተገብቶለት ከነበረው 100 ሚሊዮን ብር መካከል 10 ሚሊዮን ብር ብቻ ገቢ መደረጉን አስታውቋል። ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በገጠመዉ የገንዘብ እጥረት ምክንያት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አካሄዶ እንደነበር ይታወቃል። በዚህም በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገዉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ተቋማት እና ግለሰቦች እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለማዕከሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ባለቤት እና ዳይሬክተር ቢኒያም በለጠ ተናግሯል።

ሆኖም ግን በተቋማት እና በድርጅቶች ቃል ከተገባው 100 ሚሊዮን ብር መካከል 10 ሚሊዮን ብር ብቻ ለማዕከሉ ገቢ መደረጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ብሎም በአገራችን በመከሰቱ ተቋማት እና ድርጅቶች ቃል በገቡት መሠረት ለማዕከሉ ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል። ቃል በተገባው መሠረት ለማዕከሉ ገቢ ያልሆኑ ገንዘቦችን ለመቀበል ምንም አይነት ጥረጥ እያደረጉ አለመሆናቸውንም አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች። በይፋ ቃል በተገባው መሠረት ገቢ ባለመደረጉ ማዕከሉ ከፍተኛ ለሆነ የገንዘብ ቀውስ መዳረጉን ጨምረው ተናግረዋል።

ማዕከሉ ቃል የተገባለትን ሙሉ ገንዘብ ቢያገኝ በርካታ ሰዎችን ከጎዳና ላይ ማንሳት ይችል እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም ማዕከሉ የጀመራቸዉን ዕቅዶች ከግብ እንዲያደርስ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረው ነበር ብለዋል። እንደዳይሬክተሩ አባባል በማዕከሉ ተጀምረው ያላለቁ ህንጻዎች በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፉ በከፍተኛ መጠን ይረዳ ነበር። ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ባገኘው ጥቂት ገንዘብ ለአረጋዊያንና አእምሮ ህሙማን የሚሆን የመኖሪያ ቤት፣ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ህንጻ መገንባቱን ቢኒያም ያስታውሳሉ።

ከዚህ ባለፈ ዳይሬክተሩ የታካሚዎችን ከፍተኛ ወጪ ለመቀንስ ታስቦ ምቹና ለ 10 ሺሕ ሰዎች የሚሆን ህንጻ በአያት አካባቢ እያስገነባ እንደሚገኝ የነገሩን ሲሆን፣ አክለውም ማዕከሉ የጀመራቸውን ሥራዎች በዘላቂነት ለማስቀጠል እና ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመቀረፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል። አያይዘውም ማዕከሉ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት በሚል መንግሥትንና ሌሎች ድርጅቶችን ሥራዎቹን እያስጎበኘ እንደሚገኝ ሳይጠቅሱ አላለፉም። በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተገኝተው የተጀመረውን የህንጻ ግንባታ ተመልክተዋል።

ህንጻው እስኪጠናቀቅ መሥሪያ ቤታቸውን ወክለው የተቻለውን ድጋፍ ለማዕከሉ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ በተዘጋጀው የቃልኪዳን ሠነድ ላይ ሚኒስትሩ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል፣ የመቄዶኒያ አረጋዊያን እና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አሁን ካለበት ከአያት በተጨማሪ በመላ አገሪቷ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሉ አረጋውያንን እና የአእምሮ ህሙማንን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም ሲባል በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ቅርንጫፍ ማዕከላትን ለመክፈት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ይህንንም ከግብ ለማድረስና ማዕከሉን ለማስፋፋት የህንጻ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ቢኒያም ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here