በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝ ሕግን የተከተለ ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።
የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በአፋጣኝ ሊለቀቁ እንደሚገባም አስታውቋል።
ሰኔ 23፣ 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር የሚገኙትን በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄ እና ምህረት ገብረክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ኢሰመኮ አስታውቋል።
እነዚህ መካከል ሦስቱን እና አንድ ሌላ ታሳሪን ጨምሮ አራት እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ መለቀቃቸውንና ቀሪዎቹ ታሳሪዎች በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ ስራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ ማስታወቁንም ኢሰመኮ ገልጿል።
ቢሆንም ግን ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱንና ታሳሪዎቹን ለመጎብኘት አለመቻሉን፤ እንዲሁም ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው ኮሚሽኑን እጅግ የሚያሳስበው መሆኑን በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
“በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑና በእስር ያሉ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት ፈጽሞ ሊከለከሉ የማይገቡና፤ ተጠርጣሪዎች በሕይወት መኖራቸውንና አካላዊ ደኅንነታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሰረታዊ የሕግ ጥበቃዎች ናቸው” በማለትም አሳስቧል።
ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አሁንም በእስር ያሉ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
እንዲሁም የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና፣ ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ሕግን ያልተከተለ ማንኛውም አይነት እስር በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚኖርን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር ሙሉ በሙሉ መቆም ያለበት ተግባር መሆኑን” ገልፀዋል።
“ታሳሪዎቹን ለመጎብኘትና የአያያዛቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል” ሲሉም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።



