ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም የደንበኞቹ ቁጥር 56 ነጥብ 2 ሚሊየን መድረሱን ገለጸ።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 56 ነጥብ 5 ቢለየን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ በዚህም የእቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀሙን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት ፥ የደንበኞች ቁጥር በበጀት ዓመቱ ከተያዘው እቅድ108 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም 22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 70 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት 26 ነጥብ 6 ቢሊየን ብሩ ለግብር ክፍያ እና 29 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ደግሞ ለተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች የተከፈለ መሆኑ ተመላክቷል።
በ2018 በወር የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ 5 ነጥብ 98 ሚሊየን ብር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 14 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ማሳደግ ተችሏልም ነው የተባለው።
የቴል ብር ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 6 ነጥብ 5 ሚሊየን መድረሱም ተገልጿል።
ተቋሙ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣትም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች 847 ሚሊየን ብር ድጋፍ መድረጉንም ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በዓመቱ ለ103 ከተሞች የ4ጂ እን የ4ጂ አድቫንስድ አገልግሎት ለማስጀመር ታቅዶ ለ68 ከተሞች ማዳረስ ተችሏል። በተቀሩት ከተሞች ላይም በቀጣይ የማስጀመር ስራዎች ይሰራሉ መባሉን ፋና ዘግቧል።




