በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፦ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን

0
858

በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና በአስቸኳይ ጥቃቱ ሊቆም እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ አሳሰቡ።

ኮሚሽነሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ደህንነትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ እጅግ በጣም እያሳሰባቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል የተካሄደው የሰላም ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ አንስቶ ስደተኞቹ  በሁለት ተዋጊ አካላት መሃል ለመውደቅ መገደዳቸውን፣ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መውደማቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ዳግም ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ኤርትራውያን ስደተኞች በአንድ ወይም ሌላ ወገን ደጋፊነት ተፈርጀው የበቀል ጥቃት እየደረሰባቸው እንዲሁም ተጠልፈው እየተወሰዱ እና እየተያዙ ስለመሆኑ የተጣሩ እና በማስረጃ የተደገፉ ሪፖርቶች ለኮሚሽኑ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

በማይ አይኒ እና በአዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ በተለያዩ ታጣቂዎች በተለይ ማታ ማታ የሚፈፀሙ አጠቃላይ የወንጀል ድርጊቶች በእጅጉ ረብሸውኛል ሲሉም ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት ሽሬ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ለእስር ተዳርገዋል፤ በመቐለ የሚገኙ ባለስልጣናትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የታሰሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በጣም ከባድ የሆኑ የኃይል ጥቃቶች እየደረሱ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየደረሷቸው መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ፣ የፌደራል መንግሥትም ሆነ በትግራይ ክልል ያሉ አካላት በእነዚህ ተዓማኒ ክሶች ላይ መደበኛ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።

የኤርትራ ስደተኞች አመጽ እና ማስፈራራት መቆም አለበት፤ ስደተኞች ዓለም አቀፍ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው እና መብት ያላቸው ሲቪሎች ናቸው ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UNHCR) የሁሉንም ወገኖች እና ተዋንያን ዜጎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ህጋዊ ግዴታቸውን መወጣት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ነጥቦችን ለማስቆጠር ስደተኞችን መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ ያቀርባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የእርዳታ ቁሳቁሶችን በማድረስም ሆነ ተጨማሪ ከፍተኛ ሰራተኞችን በማሰማራት ምላሹን እያሳደገ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ኤርትራዊያን ስደተኞችን ጨምሮ ሲቪሎችን መጠበቅ እና የሰብአዊ ዕርዳታን የማድረስ ጥረትን ለማቀላጠፍ የበለጠ ጥረት በአስቸኳይ ከሁሉም ወገኖች ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here