በወደቦች ላይ የተከማቹ ዕቃዎችን ግለሰቦች በራሳቸው እንዲያነሱ ፈቃድ ተሰጣቸው

0
1042

በቻይና ወደቦች ላይ የተከማቹ ዕቃዎችን ለማንሳት 13 ሺሕ ኮንቴይነር ያሰፈልጋል

ከፍተኛ የሆነ የኮንቴነር እጥረት በመከሰቱና የመርከብ ኪራይም በመጨመሩ ምክንያት በተለያዩ የቻይና ወደቦች ላይ የተከማቹ ዕቃዎችን ግለሰቦች በራሳቸው እንዲያነሱ ፈቃድ መሰጠቱን የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።
የኮንቴይነር ችግርን በዋናነት እንዲባባስ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከቻይና ወደ አሜሪካ እና ሰሜን አውሮፖ የሚጓጓዝ የጭነት መጠን እየጨመረ መምጣቱ ነው። በሌላም በኩል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝም ሌላው ምክንያት መሆኑን የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አሸብር ኖታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም ይህ የባዶ ኮንቴነር እጥረት በአገራችን የገቢና የወጪ ንግድ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሌላው ችግሩን ካባባሱት ጉዳዮች መካከል የክረምቱ ወቅት መሆኑን ያነሱት አሸብር፣ ይህ የክረምት ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት በመሆኑ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል። በአሁኑ የክረምት ወቅት ንግዱ በአራትና በአምስት እጥፍ በመጨመሩ ችግሩ ውስብስብ እንዲሆን አድርጐታል ሲሉ አብራርተዋል።

እነዚህ ችግሮች ተደማምረው ወደ አገር ውስጥ በሰዓቱ መግባት ይኖርባቸው የነበሩ ዕቃዎች ቻይና ወደብ ላይ ሊከማቹ መቻላቸውን አስረድተዋል።
በወደብ ላይ የተከማቹትን ዕቃዎች ለማንሳት በትንሹ ድርጅቱ ከ13ሺ በላይ ባዶ ኮንቴይነር ማግኘት ይኖርበታል ሲሉ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
አያይዘውም ችግሩ የተከሰተበት የቻይና ወደብ ከፍተኛ የገቢ ዕቃ የሚመጣበት መሆኑን አንስተው በሌሎች አከባቢዎች ላይ ችግሩ እንዳልተስተዋለ ተናግረዋል።
ይህን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለ ንብረቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

በላኪዎች እና አስመጪዎች ላይ ሊከሰት የሚችለውን ኪሳራ ለመታደግ፣ ግለሰቦቹ በሚመቻቸው መንገድ ከወደቡ ላይ ዕቃቸውን እንዲያነሱ የሚያስችላቸው ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።
ፈቃዱ በዋናነት ድርጅቱ ዕቃዎችን ለማንሳት አቅም ካጣ እና ግለሰቦቹ በራሳቸው የኪራይ መርከቦችን እና ኮንቴይነሮችን በመጠቀም ዕቃዎቻቸውን እንዲያነሱ የሚያስችል ዕውቅና እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም ረገድ በርካታ ደንበኞች ከድርጅቱን ባገኙት ፈቃድ መሰረት ከወደቡ ላይ ዕቃዎቻቸውን እያነሱ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል፣ ድርጅቱ ለነዚህ ችግሮች ካስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ ውስጥ እንደየሁኔታው ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚጓጓዝ ዕቃ እንዳለ ተገልጿል።
ለምሳሌ ያህል፣ ወደብ ላይ በመቆየታቸው ብቻ የሚበላሹ እንደ መድኃኒት፣ ምግብ ነክ የሆኑ እና አንገብጋቢ የተባሉ ሸቀጦች ቅድምያ ተሰጥቷቸው እንዲጓጓዙ ይደረጋል ተብሏል።
ይህንንም ችግር ለመፍታት ድርጅቱ ያሉትን ኮንቴይነሮች በሙሉ ዕቃዎቹ ተከማችተው ወዳሉባቸው አካባቢዎች የማሰማራት ሥራ እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ችግሩ በስፋት በሚገኝባቸው የቻይና ወደቦች ላይ ድርጅቱ የራሱንና ሌሎች በኪራይ ያመጣቸውን መርከቦች በመጠቀም በከፍተኛ ፍጥነት ክምችቱን እያቃለለ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንኑ ተግባር በማጠናከርም ቀሪ ክምችቶችን እስከ ነሐሴ አጋማሽ 2013 ድረስ አጠናቆ ከወደቦቹ ለማንሳት እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተያያዘ ዜና በዚህ ፈታኝ ወቅት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎችን ኹሉ በማለፍ በበጀት ዓመቱ ድርጅቱ ሊያነሳቸው ካቀደው 17ዐ ሺሕ ሙሉ ኮንቴይነሮች 15ዐ ሺሕ በማንሳትና ዕቅዱን በማሳካት በቀጠናው ውጤታማ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።
እንደ አሸብር ገለጻ፣ ደርጅቱ ቀሪዎቹን በዓመቱ ዕቅድ ውስጥ የተያዙና በተገለጸው ምክንያት መጫኛ ወደቦች ደርሰው ያልተነሱ ጭነቶችን በማንሳት፣ እንዲሁም በክረምቱ ወራት ተጨማሪ ጭነቶች በፍጥነት እንዲነሱ በማድረግ በነሐሴ ወር መጨረሻ ወደ መደበኛ አሠራሩ ይመለሳል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በድርጅቱ ሥራ ላይ ጫና ያሳረፉ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የተከሰቱ ቢሆንም፣ ድርጅቱ በራሱ አቅምና ሌሎች የመርከብ ወኪሎችን በመጠቀም የተቀናጀና አስፈላጊ አገልግሎት ለደንበኞቹ ሳይቋረጥ አድርሷል ተብሏል። በዚህም የአገር ኢኮኖሚ ምንም እንከን እንዳያጋጥመው የራሱን የሆነ ድርሻ የተጫወተበት እና ወቅቱም ድርጅቱ ጥንካሬውንና የአገልግሎት አቅሙን ያሳየበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here